በሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስር የሚገኙ ክላስተር ማዕከላት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው
በሃዋሳ ከተማ ክሬሸር ክላስተር ማዕከል በኢ ኤም ቲ አይ የፈጠራ ስራ ማህበር ፓቶን የተሰኘ ጀልባ የሰራ ሲሆን ማህበሩ ከዚህ ቀደምም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 58 ያህል የፈጠራ ስራዎችን አምርቶ ለገበያ አቅርቧል፡፡ የትራፊክ መብራት ፣የቆጮ ማቀነባበሪያ ማሽንና ፓቶን ጀልባ ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኢ ኤም ቲ አይ የፈጠራ ስራ ማህበር የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የማህበሩ ስራ አስኪያጅና የፓቶን ጀልባ ፈጠራ ባለቤት ወጣት ኢንጂነር በረከት መስፍን ገልጻል ፡፡ በኢ ኤም ቲ አይ የፈጠራ ስራ ማህበር በወጣት ኢንጂነር በረከት መስፍን የተመረተው ፓቶን ጀልባ ስፋቱ 15 ሜትር በ4 ሜትር ነው ፡፡ ጀልባው በፀሐይ ብርሃን( Solar ) የሚሰራ ሲሆን በአንድ ጊዜ 60 ሰዎችን ማጓጓዝ የሚችል መሆኑን የፈጠራው ባለቤት ተናግሯል ፡፡ ፓቶን ጀልባ በአሁኑ የገበያ ዋጋ ግምቱ 1.8 ሚሊየን ብር ሲሆን ለ36 ያህል ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር እንደሚችልም ታውቋል ፡፡ የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስፈጻሚና የፓርኮች ኦፕሬሽን አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ዬተራ ሀዋሳን ጨምሮ በክልሉ ባሉት አራት የክላስተር ማዕከላት በማህበርና በግል ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ደረጃ አንቀሳቃሾች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ያላቸው ሚና እየጎላ መምጣቱን ጠቅሰው በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ከኮርፖሬሽኑ የሚጠበቀው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ፡፡