የካቲት 02/06/2015 ዓ.ም
ወቅታዊ ክልላዊ ጉዳይን አስመልክቶ ከሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ የተሰጠ የአቋም መግለጫ፦
የሲዳማ ህዝብ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን በመዋቅር ደረጃ ካረጋገጠ ሶስት አመታት አልፎታል። በዚህ ሶስት አመታት ውስጥ የተቋቋመው የክልሉ መንግሥት አስፈላጊ መዋቅሮችን ዘርግቶ፣ የሰው ሀይልን እውቀትን፣ ክህሎትንና ስነምግባርን መሠረት ባደረገ መልኩ አደራጅቶ፣ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ፣ የደሞክራሲና የፍትህ ጥያቄዎች ከመመለስ ይልቅ፣ በየመድረኩና በየሚዲያው ህዝቡ ታግሎ እውን ያደረገውን ክልል እንደ ክልሉ አመራር የስራ አፈፃፀም ተደርጎ መልሶ ለህዝቡ መተረክ፣ የተደራጀ የውሸት የልማት ሪፖርት ማቅረብ፣ የህዝቡን አንድነት መሸርሸር፣ ጎሰኝነትንና ቡድንተኝነት ማስፋፋት፣ አድሎአዊ አሰራር መከተል፣ የህዝቡን ቋንቋና ባህሉን ለማሳደግ ትኩረት አለመስጠት፣ ሀሳብን የመግለጽ ደሞክራሲያዊ መብትን ማፈን፣ ህዝቡን ለህገወጥ እስራትና ስደት መዳረግ፣ ከፍተኛ ሙስናና ብልሹ አሰራር፣ ለፍትህ እጦትና የተለያዩ ማህበራዊ ቀውስ የክልሉ አስተዳደር መገለጫዎች ሆነው ቆይተዋል።
በተመሳሳይ ሁኔት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፦
1. በክልሉ አመራር የሚደረጉ መድረኮች በተመለከተ:- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ አመራር የሚደረጉ መድረኮች ከህግና የኢትዮጵያነት ጨዋነትም ሆነ የሲዳማዊነት እሴት ባፈነገጠ መልኩ ስድብና ዛቻ የተሞላበት እየሆነ መምጣቱ አሳስቦናል። በተለይም በቅርቡ በመንግስት ከፍተኛ መድረክ ሚዲያዎች ባሉበት ህዝቡን በይፋ መሳደብ፣ ክብሩን የማይመጥን ሎአላዊነቱን የሚጋፉ ንግግሮች በይፋ ሲደረጉ ተገንዝበናል።
በተለይም የህዝብን ስልጣን ባለቤትነት በሚፃረር ፣ የመሪን አምባገነንነት በሚያሳይና የህዝባችንን ጀግንነትና ክብር በሚያሳንስ መልኩ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድርን "የሲዳማ ህዝብ ይፈራሃል" የሚልና የህዝቡን ክብር የማይመጥን ንግግሮች ከመድረኩ መነሳቱ ለምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።
2. የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ያለፈቃድ መቁረጥን በተመለከተ:- ለሀገር ደህንነት ወይም ለከልሉ ልማትና ደህንነት ሲባል ዜጎች ከገዛ ሀብታቸው ወይም ከደመወዛቸው በፈቃደኝነት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህ የሚሆነው ግን ህግንና ስርዓቱን በተከተለ መልኩና እንዲሁም ሌላ ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ቀውስ በማያስከትል መልኩ ነው። አሁን በሀገርም ይሁን በክልል ደረጃ የኑሮ ውድነቱ ቀውስ የዜጎችን ህይወት እየተፈታተነ ባለበት በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥት ህገወጥ በሆነ መልኩ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ያለፈቃዳቸው እየተቆረጠ መሆኑን ተገንዝበናል።
3. የክልሉ ከልክ ያለፈ የስራ አጥነት ቀውስ በተመለከተ:- በክልሉ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ስራ አጥ ወጣቶች አሉ። በሀገር ደረጃ የስራአጥነት ቀውስ መኖሩ የሚታወቅ ነው። ነገር ግን በክልሉ የሚታየው ከልክ ያለፈ የስራ አጥነት ቀውስ የሀገራዊ የስራ አጥነት ቀውስ አካል ብቻ ሳይሆን በክልሉ የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሙስና፣ ብልሹና አድሎአዊ አሰራር ውጤት ጭምር እንደሆነ ፓርታያችን ያምናል። በተጨማሪም የክልሉ መንግሥት ይህንን ችግር በአግባቡ መርቶ ከመቅረፍ ፈንታ "ስራ አጥነት የለም" የሚል ክህደታዊ ትርክት በየመድረኩ ስያፀባርቅ መታየቱ ችግሩን አምኖ ተቀብሎ ለመፍታት ዝግጁ ያልሆነ መስሎ ይታያል።
ከዚያም አልፎ በክልሉ መንግስት ስራ አጥ ወቶች የመብት ጥያቄ በሚያነሱበት ጊዜ በአግባቡ ከማነጋገር ይልቅ አፍኖ ማስርና ማሳደድ የተለመደ አካሄድ ሆኗል። በሌላ በኩል ችግሩን በዘላቂነት ከመፍታት ይልቅ ጥያቄውን አበክረው ለሚያነሱት ወጣቶች ለማዘናጋት ብቻ ሲል አግባብ ያልሆነ አበል ወይም ጊዜያዊ መደለያ መስጠት የተለመደ ሆኗል።
4. ሙስና፣ ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር እጦት በተመለከተ፦
-በሲዳማ ክልል ከፍተኛ የተደራጀ ሌብነት የሚታወቅ ሆኗል። ለምሳሌ፦ ቡና መፈልፈያ ኢንዱስትሪ ፈቃድ አሰጣጥ ከፍተኛ ሌብነት እና የግልጽነት ጉድለት የሚስተዋልበት፣ የከተማ መሬት ወረራ፣ በኢንቨስትመንት ሽፋን ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር የሚደረግ የሀብት ዝርፊያ፣ ኮንትሮባንድ፣ ወዘተ የክልሉ መገለጫ ሆኖ ቆይቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሙስናን ለመዋጋት በሀገር ደረጃ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አካል ነው ተብሎ በክልሉ የተቋቋመው ኮሚሽን ከሌብነት ነፃ ያልሆነና ሌብነት መኖሩን እንኳን በቅጡ የማያምን መሆኑ የአደባባይ ምስጥር ነው።
5. የክልሉ መንግሥት የክልሉን ህዝብ የመደራጀት መብት ለመገደብ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ:-
በፖለቲካ ስረዓት ውስጥ አንድን ህዝብ ለመጨቆንና አምባገነናዊ ስርዓት ለመዘርጋት ከተፈለገ የህዝቡን በፖለቲካ የመደራጀት መብት መገደብ ነው። በተለይ ጠንካራ ተፎካካሪና የተደራጀ አማራጭ ሀሳብ ለህዝቡ የሚያቀርብ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይደራጅ ማድረግ የአምባገነናዊ ስረዓት መገለጫ ነው። ሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ የሀገሪቱን ህገመንግስታዊ የመደራጀት መብት ተጠቅሞ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሙሉ እውቅና አግኝቶ ህጋዊ ሰውነት ወስዶ ወደ ስራ የገባ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ ነው።
የክልሉ መንግሥት ይህ ፓርቲ እንዳይቋቋም በርካታ መሰናክሎችን ሲያዘጋጅና ሲተገብር መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ፓርቲው ተቋቁሞ፣ ህጋዊ ሰውነትንና ሙሉ እውቅና አግኝቶ የአደረጃጀትና የአባላት ምዝገባ በሚያደርግበት በአሁኑ ወቅቱ ይህንን ህጋዊና ህገ-መንግስታዊ እንቅስቃሴ ለመገደብ ተንቀሳቅሷል።
በእጃችን ያለው ማስረጃ እንደሚያሳየው አንዳንድ ወረዳዎች የፓርቲው ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች እንዳይከፈቱ በይፋ እያገደ እንደሆነ ነው። ለምሳሌ፦ በሁላ ወረዳ ፖሊስ "ቅርንጫፍ ፅ/ቤት እንዳይከፈት ከልክሉ የሚል ትዕዛዝ ከክልሉ ስለተሰጠን መክፈት አትችሉም" በማለት የፓርቲውን ታፔላ በማንሳት በፓርቲ አመራሮችና አስተባባሪዎች ላይ ወከባና ዛቻ ፈፅሟል።
በጥር 23/05/2015 ዓ.ም በሆሮሬሳ ወረዳ የፓርቲ ቅርጫፍ ፅ/ቤት የፓርቲውን ታፔላ በማንሳት አስር የፓርቲው አስተባባሪቻችን አስረዋል። በጥር 24/05/2015 የታሰሩ አስተባባሪዎቻችንን በህገወጥና በኢ-ሰብዓዊ አካሄድ ከምሽቱ 5:30 ገደማ ከታሰሩበት ፖሊስ ጣቢያ ድብደባ እየፈጸሙባቸው ወደ በንሳ ማረሚያ ወስደው ካሳደሩ በኋላ ጥር 25/2015 ከማረሚያ አውጥተው ቤተሰቦቻቸው እንኳን በቅርበት ወደማያገኙበት ሀዋሳ ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረዋል። ሌሎች የተለያዩ ወረዳዎችም ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ የሆኑ ክልከላዎች ተፈፅሞብናል።
ስለሆነም ሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ የሚከተሉትን ባለ አምስት ነጥብ አቋም መግለጫ አውጥቷል፦
1. በክልሉ መንግስት በየመድረኩና በየስብሰባው የህዝቡን ክብርና ሉአላዊነት የማይመጥን፣ የሲዳማዊነት እሴትንና የኢትዮጵያዊነት ጨዋነትን በተፃረረ መልኩ በህዝቡ ላይ የሚደረግ ስድብና ዛቻ እንዲቆም እንጠይቃለን።
2. የክልሉ መንግስት በህገወጥ መንገድ ያለ ሰራተኞች ፈቃድ እየቆረጠ ያለው የክልሉ የመንግሥት ሰራተኞች ደመወዝ ከህገወጥነቱ አልፎ ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትል በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆምና በህገወጥ መልኩ የተሰበሰበውም ደመወዝ ለሰራተኞች ተመላሽ እንዲሆን እንጠይቃለን።
3. የክልሉ መንግሥት በክልሉ የሚታየውን ልክ ያለፈ የስራ አጥነት ቀውስ ከመካድ ማመኑ ለመፍትሔውም ይሁን ለስራ አጡ ወጣት ሞራልም የተሻለ እንደሆነ እናምናለን። በተለይ ቀውሱ በክልሉ ጎልቶ የሚታይበት ዋና ምክንያቶች፦ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ሙስናና የብልሹ አሰራር ወጤት ጭምር ስለሆነ ፍትሀዊ አሰራር መዘርጋት ቀውሱን ለመቀነስ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን። ስለዚህ የክልሉ መንግሥት ክህደትን፣ አፈናና ጊዜያዊ መደለያ እንደ መፍትሔ አድርጎ መውሰዱን አጥብቀን እንቃወማለን።
4. ሙስናን ከመዋጋት አንፃር በቅርቡ በክልሉ የተቋቋመው ኮሚሽን "አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ" ከሚባለው አይነት ተረት የሚመሳሰል ስለሆነ በሲዳማ ክልል እየተፈፀመ ያለው ከልክ ያለፈ ዝርፊያ በፌደራል መንግስት ወይም ሌላ ገለልተኛ አካልና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲመረመር እንጠይቃለን።
5. በክልሉ ህገ-መንግስታዊ የመደራጀት መብትን ለማስተጓጐል ብሎም ለመገደብ የሚደረግ መንግስታዊ ህገወጥና ኢ-ህገመንግስታዊ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ሲዳማ ፈዴራሊስት ፓርቲ
የካቲት 02/06/2015 ዓ.ም
ሀዋሳ
Comments
Post a Comment