የአገር ውስጥ ግብይት ከዓለም ዋጋ የበለጠ መሆኑ አንደኛው ምክንያት ነው ተብሏል
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት የቡና ወጪ ንግድ፣ በዚህ ዓመት ለመላክ ከታቀደው መጠን በታች አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ። ይህንን በማስመልከት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ባደረገው ጥናት፣ 181 ላኪዎች ወደ አውሮፓ አገሮች ቡና ሊልኩ 288 ውሎችን ቢፈጽሙም መላክ አልተቻለም ተብሏል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዘጋጅነት የግብርና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የስድስት ወር ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ሰኞ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ተካሂዶ የነበረ ሲሆን፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ኃላፊዎችም ከቋሚ ኮሚቴው አባላት የቡና ወጪ ንግድን በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ማብራርያ ሰጥተዋል።
አብዛኞቹ በአውሮፓ የሚገኙ የቡና ገዥ አገሮች የገቡዋቸውን ኮንትራቶች በመሰረዛቸው፣ ተዘጋጅቶ የቀረበውን ቡና ባለመውሰዳቸውና በዋነኝነትም ዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ በመቀነሱ፣ ኢትዮጵያ ለመላክ ያቀደችው የቡና መጠን ሊቀንስ መቻሉን የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ዑመር በምክር ቤቱ ለተገኙት የቋሚ ኮሚቴ አባላት አብራርተዋል።
አቶ ሻፊ በማብራሪያቸው ባለሥልጣኑ ጥናቱን ባካሄደበት የበጀት ዓመቱ የመጀመርያ አምስት ወራት ለመላክ የታቀደው የቡና መጠን 137 ሺሕ ቶን ቢሆንም፣ የተላከው ግን 109 ሺሕ ቶን ቡና ነው ብለዋል። ቀሪው 28 ሺሕ ቶን ቡና በተሰረዙት ውሎች ውስጥ ታቅዶ እንደነበር አክለዋል።
‹‹ባካሄድነው ጥናት መሠረት የኮንትሮባንድም ሆነ ቡና የማጣት ችግር ሳይሆን፣ ለዚህ መንስዔው የዓለም ቡና ዋጋ መውረድ ነው፤›› ሲሉ አቶ ሻፊ የአገሮች የመግዛት አቅም ማነስን እንደ ትልቁ ችግር ገልጸዋል። ‹‹ቡናችን በስፋት ወደ አውሮፓ እንደ መሸጡ፣ በአውሮፓ ያሉ አገሮች ባጋጠማቸው ችግር ከዚህ በፊት የገቡትን ኮንትራት ሰርዘዋል፤›› ብለዋል።
ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የዓለም ቡና መሸጫ ዋጋ የዓለም አቀፍ የቡና መጠን መለኪያ በሆነው በፓውንድ 2.5 ዶላር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት በአንድ ዶላር ወርዶ 1.5 ዶላር እየተሸጠ ነው። በኪሎ ግራም ደግሞ ወደ ሁለት ዶላር ወርዷል።
አቶ ሻፊ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ላነሷቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ፣ የቡና የአገር ውስጥ ግብይት ዋጋ ከዓለም አቀፍ ዋጋ የበለጠ መሆኑም አንደኛው ወደ ውጭ በተፈለገው መጠን ላለመላክ ምክንያት ነው ብለዋል። ‹‹በአገር ውስጥ የሚሸጥበት ዋጋ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ፣ የዓለም ዋጋና የአገር ውስጥ ዋጋ ያለመናበብ ሌላኛው ችግር ነው፤›› ሲሉ አቶ ሻፊ ጠቁመዋል።
የቡና ወጪ ንግድ አፈጻጸም ከመጠን አኳያ ቅናሽ ቢያሳይም ያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ላይ ግን ለጊዜው ማነስ ያልታየበት፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀርም የ80 ሚሊዮን ዶላር (14 በመቶ) ብልጫ ያለው መሆኑ ተጠቅሷል። እንደ አቶ ሻፊ ገለጻ፣ የቡና ገቢ እንደ መጠኑ ዝቅ ያላለበትን ምክንያትም ኢትዮጵያ የምትልከው ቡና ጥራት እያደገ በመምጣቱና ዋጋው ከፍ ያለ በመሆኑ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፈው የበጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ካገኘችው 4.1 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ውስጥ በቡና የተገኘው አንድ ሦስተኛውን የሚሸፍን ስለነበር፣ ቡና ለአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ የማስገኘት አቅም ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። ‹‹እንደተባለው ነገሩ አሳሳቢ ነው፣ ግን ችግሮችን ለመቅረፍ እየጣርን ነው፤›› ሲሉ አቶ ሻፊ የመሥሪያ ቤታቸውን ጥረቶች ዘርዝረዋል።
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ አንደኛው ኮንትራቶቹ እንዳይሰረዙና የ181 ላኪዎች ቡና መውጣት እንዳለበት ግፊት ማድረግ ነው። በተጨማሪም አዳዲስ ገበያዎችን የመፈለግ ስትራቴጂ መንደፍ ይገኝበታል።
‹‹ነባር ገበያዎች ችግር ስላጋጠማቸውና አዳዲስ ገበያ ውስጥ መግባት ስላለብን እንደ ቻይና፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ታይዋን ዓይነት ገበያዎችን እየፈለግን እየገባን ነው። አንደኛ ገዥያችን ጀርመን ነበረች፣ አሁን የጀርመን የመግዛት አቅም እየወረደ ስለሆነ ቡናውን ወደ ሌላ ገበያ እንዲሄድ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል፤›› በማለት ባለሥልጣኑ እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት አስረድተዋል።
Comments
Post a Comment