ሀዋሳ ጥር 11/2015 (ኢዜአ) በሀዋሳ የጥምቀት በዓል እየተከበረ ይገኛል ።
በደብረ ምጥማቅ መድኃኔዓለም ቤተክስትያን እየተካሄደ ባለው የጥምቀት ክብረ በዓል ላይ የሲዳማ ፣የጌዴኦ ፣አማሮና ቡርጂ እንዲሁም የምዕራብ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ተገኝተዋል ።
እንዲሁም የሲዳማ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መርጊያ ሌሊት በማህሌትና ቅዳሴ ሥርዓት ሲያመሰግኑ ያደሩት የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንትና በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል ።
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ በሰጡበት ወቅት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባህረ ዮርዳኖስ የተጠመቀው የሰው ልጆችን የዕዳ ደብዳቤ በመደምሰስ ከባርነት ቀንበር ነፃ ለማውጣት ነው ብለዋል ።
በክርስቶስ ያገኘነውን ነፃነታችንን ጠብቀን ለመኖር ራሳችንን መግዛትና ከክፋት ማራቅ ይጠበቅብናል ነው ያሉት ።
ሠላምና ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርን መስጠትን ዋንኛ የሕይወት መርህ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል ።
ሥልጣን፣ ዝናና ሀብትን በመጠቀም ሌሎችን ከመበደል መራቅ በተለይ ለተቸገሩ ዜጎች የሚራራ ልብ ያስፈልገናል ብለዋል ።
በአቋራጭ ለመክበር ከሚደረግ ጥረት ከሌብነት ፣ ከሀሰት ፣ ከመለያየትና እርስበርስ ከመጨካከን ራስን ማቀብ ያሻል ነው ያሉት ።
ኢትዮጵያ የቀደመ የአብሮነትና አንድነት እሴቶቿ ተጠብቀው ፅኑ ሀገር ሆና እንድትቀጥል እርስ በርስ ከመገፋፋትና ከመጠላላት ይልቅ መከባበርና መዋደድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል ።
የሲዳማ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መርጊያ የጥምቀት በዓል ከሐይማኖታዊ አስተምህሮቱ ባሻገር የኢትዮጵያን አንድነትና ትሥሥር የሚያጠናክሩ ማህበራዊ ኩነቶች በውስጡ መያዙንጠቅሰዋል ።
የሀገርን ገፅታ በበጎ መልኩ በማጉላት ከፍተኛ ሚና እዳለው ተናግረዋል ።
የዓለም ቅርስ የሆነው ይህ በዓለ ጥምቀት ሐይማኖታዊና ማህበራዊ ትውፊቶቹ ተጠብቀው እንዲቀጥሉ ብሎም ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘው ጥቅም እየላቀ እንዲሄድ በትብብር መስራት እደሚያስፈልግ አስረድተዋል ።
በበዓሉ አከባበር ላይ የተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም ታድመዋል ።
Comments
Post a Comment