በዛሬው ዕለት በሲዳማ ክልል ዝግ ግምገማ ይካሄዳል ፤
======================================
አፊኒ ጥር 12 2015 ዓ.ም
ሐዋሳ
ባሳለፍነው ሳምንት በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በሃገራዊ፣ ወቅታዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሁለት ቀን መምከሩ ይታወሳል።
በዚህ መድረክ መጀመሪያ ቀን በርካታ የክልሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ በተለይ ህዝቡን ያስቆጡ ንግግሮችና ዘለፋዎች የክልሉ መንግስት በሚመራቸው ሚዲያዎች ጭምር ተሰራጭቷል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች በዋናነት የህዝብን የስልጣን ሉዓላዊነት ላይ ያነጣጠሩና የህዝቡን የነፃነት ትግል ያላማከሉ ንግግሮች ተደምጠዋል። ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ በተጨባጭ ካለው ችግር በተቃራኒ ግለሰቦችን ያነጣጠረ ስድብና ዘለፋ ብቻ ሳይሆን ዛቻ ጭምር ከመድረኩ መሪዎች እስከ ውይይቱ ተሳታፊዎች ተሰንዝረዋል።
የክልሉ ፕረዚዳንት ከስልጣን እንደተነሳ ስለተነሳው ጉዳይ፣ እሳቸው ከስልጣን እንዳልተነሱና ከስልጣን ቢነሱ እንኳ የተሻለ ስልጣን እንደሚጠብቃቸው ገልፀው፣ ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
በውይይቱ ስራአጥነት አንዱ የመወያያ ነጥብ የነበረ ቢሆንም፣ አመራሩ ስራአጥነትን በውሸት ሪፖርት አድበስብሰው ለማለፍ ያደረጉት ነገር ብዙዎችን ያሳዘነ ነበር። በክልሉ ተመርቀው ከ4 ዓመት በላይ ስራአጥ ሆነው እየተንከራተቱ ያሉ ብዙ ወጣቶች ባሉበት፣ ብዙ የስራ ዕድል ተፈጥሯል ተብለው በተለይ በወረዳ አስተዳዳሪዎች የተነሳው ጉዳይ፣ መንግስት ለችግሩ መፍትሔ እንዳይሰጥ እስከማስተጓጎል የሚደርስ ነው።
በሌላ በኩል የሐዋሳ ከተማ ከንቲባን በተመለከተ፣ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ እንደተገባና፣ የክልሉ ፕረዚዳንትም ከንቲባውን እንዳስጠነቀቁ አፊኒ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሌላው በውይይቱ የተነሳው የልማት ጉዳይ ነው። ልማትን በተመለከተ ህዝቡ ብዙ ጥያቄ እያነሳ የሚገኝ ቢሆንም፣ ከውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ በርካታ የልማት ስራዎች እንደተሰሩና ስለ ልማት በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚቀርቡ ጥያቄዎች ሆነ ትችቶች የልማትና ሰላም ጠል ቡድኖች ስራ ስሉ ተናግረዋል።
ይሁንና ተሳታፊዎች ይሄን ይበሉ እንጂ፣ በክልሉ ተጀምረው ሳያልቁ የቆሙ፣ ቃል ተገብተው እና መሠረተ ድንጋይ ተጥለው ወደ ስራ ሳይገባ የቆዩ፣ ለዓመታት የቆዩ የልማት ጥያቄዎች አሁንም ድረስ መፍትሄ እንዳላገኙ ከህዝቡ ከሚቀርቡልን አቤቱታዎች እና በመስክ ጉብኝት በማድረግ በተከታታይነት ስናቀርብ መቆየታችን ይታወሳል።
በሁለተኛው ቀን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተውካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ በያዙት መድረክ ሰፋ ያሉ ጉዳዮች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። በዋነኝነት ዕድል የተሰጣቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ እየሆነ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው እና አመራሩ ለሁለት ፓለቲካ ጎራ እንደተከፈለ የቀድሞ የሲዳማ ዞን ፀጥታ መምሪያ ኃላፈ በመግለፅ እራሳቸው ከሁለቱም ጎራ እንዳልሆኑ ገልፀው፣ የብልፅግና ዋና ጽ/ቤት ጣልቃ ገብቶ ህዝብን እንዲያወያይ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ መንገድ አንድ ወጣት እንደ ገለፁት፣ አሁን በክልሉ አመራር እና ህዝብ መካከል የተፈጠረው አለመተማመን በአመራሩ ውይይት ብቻ ሳይሆን ህዝባዊ ውይይት የሚፈልግ እንደሆነ በአፅንኦት ገልጿል።
ይሁን እንጂ ጠንከር ያለ ሀሳብ ላነሱ፣ ለውይይቱ ተሳታፊዎች የክልሉ ፕሬዘዳንት የእጃችሁን ታገኛላችሁ አዘል ምላሽ እንደሰጧቸው ለአፊኒ ከውስጥ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
እንደ መረጃ ምንጫችን በዚህ የተገረሙት አፈጉባኤው ከዚህ በፊት በኢህአዴግ ዘመን የሚደረገውን አፈና እና የሀሳብ ነፃነት አለመኖሩን ገልፀው፣ በዘመነ ብልፅግና ሰዎች በሃሳባቸው ምክንያት እንዳይሸማቀቁ ዕድል መስጠት አንዱ የብልፅግና ዋነኛው መርህ እንደሆነ በመግለፅ፣ በአሁኑ ጊዜ እሳቸው በሚመሩት መድረክ ለሃሳብ ነፃነት እየሰሩ ያሉበትን ተሞክሮ አጋርተዋል። አፈ ጉባኤው አክለውም የክልሉ ከፍተኛ አመራር እጁ እና ድርጊቱ ንጽህና ካለው ምንም ስጋት ሊሰማቸው እንደማይገባ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በዛሬው ቀን በሚኖረው መድረክ አመራሩ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ፣ ህዝብን እያማረሩ ያሉ ያለ ትምህርት ዝግጅትና የአመራርነት ብቃት በዘመድ እና በገንዘብ በተሾሙ ጥቂት በማይባሉ ባለስልጣናት ጉዳይ፣ ጎሰኝነትን እንደ ፓለቲካ መርህ አድርገው በሚንቀሳቀሱ፣ በሌብነትና ብልሹ አሰራር፣ ህዝቡን እያማረረ ባለው ኑሮ ውድነት እና በወጣቱ ስራ አጥነት ላይ የህዝብን ተጠቃሚነት ማዕከል ባደረገ መልኩ ነፃ፣ ከበቀል እና ጥላቻ የፀዳ ውይይት አድርጎ በቀጣይነት ችግሮችን ለመፍታት መስራት ይጠበቅበታል። ይህንን ተግባራዊ በማድረግ እየሻከረ የመጣውን የህዝብ እና መንግሥት አለመተማመንን ያክማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በቀጣይነትም ጉዳዮችን በቅርበት እየተከታተልን እናቀርብላችኋለን !
አፊኒ_ሚዲያና_ኮሙኒኬሽን
Comments
Post a Comment