በኢትዮጵያ ያሉ መልከ ብዙና ማራኪ ውብ ባህሎች ለ50 አመታት እዚሁ እንድኖር አድርጎኛል፣ኢትዮጵያዊያንም ያሏቸውን የአንድነትና መተሳሰብ ባህል አክብረው አገራቸውን ማስቀጠል አለባቸው ሲሉ ጣሊያናዊው የካቶሊክ ካህን ተናገሩ።
ላለፉት 50 ዓመታት ኑሯቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉት ጣላያናዊው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህን ዮሴፍ ዲቶማሾ ኢትዮጵያ የድንቅ ባህልና ታሪክ ባለቤት መሆኗን ይመሰክራሉ።
አብዛኛውን ኑሯቸውን በሲዳማ አካባቢ ያሳለፉ ቢሆንም ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው ማዬት ማቻላቸውን በመናገር ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በጌዲዮ፣ በይርጋ ጨፌ፣ በአለታ ወንዶ፣ በአገረ ማርያምና ሌሎች አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች መስራታቸውን ጠቅሰዋል።
አሁንም ድረስ በሀዋሳ ከተማና ሌሎች ገጠራማ የሲዳማ አካባቢዎችም በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት እያገለገሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ተሰባስበው የሚያከብሯቸው እንደ ‘ፊቼ ጫምበላላ’ እና መሰል በዓላትም እጅግ የሚያስደስቱና ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጣቸው መሆኑንና ፊቼ ጨምበላላ የሰላምና የፍቅር፣ የይቅርታና የእርቅ፣ የአንድነትና መተሳሰብ፣ የእድገትና ብልጽግና በዓል እንደሆነ መመልከታቸውንም እንዲሁ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ድንቅ ባህሎች እንዳሉ የጠቀሱት ካህኑ እነዚሁ በዓላት ለአብሮነት መጎልበት ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ይላሉ።
በቆይታቸውም በርካታ ባህላዊ እሴቶችን ከመረዳት ባሻገር አማርኛና ሲዳምኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው የሚናገሩ መሆኑን ኢዜአ በመረጃው አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ቆይታቸው በደስታ የተሞላ እንደሆነ የሚናገሩት ካህን ዮሴፍ በአገሪቱ ያሉ መልከ ብዙና ማራኪ ውብ ባህሎች እዚሁ እንዳስቀራቸው ይናገራሉ።
ኢትዮጵያዊያንም ያሏቸውን ውብ የአንድነትና መተሳሰብ ባህል አክብረው አገራቸውን ማስቀጠል እንደሚኖርባቸው መክረዋል።
Comments
Post a Comment