“ከዚህ በኃላ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በውሸት ሪፖርት መቀለድ አይቻልም”፦ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ********************** ከዚህ በኃላ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በውሸት ሪፖርት መቀለድ አይቻልም ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለፁ። ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሥራ ዕድል ፈጠራ የስትሪንግ ኮሚቴ የ7 ወር አፈፃፀሙን በገመገመበት ወቅት ነው። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በንግግራቸው አንድ ሰው ትምህርት የሚማረው በእውቀትና በክህሎት ሥራውን ለመስራት እንዲረዳው እንጂ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ልቀጠር ነው ብሎ መሆን የለበትም ብለዋል። ማንም ሰርቶ ነው ሀብት የሚያፈራው ለዚህም ወጣቱ ሰርቶ እንዲለወጥ ስራ መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልላችን ሥራ የሚፈልጉ ወጣቶች ቁጥር በርካታ በመሆኑ ወጣቱን ቀጥሮ ብቻ ስራ ማስያዝ ስለማይቻል የሥራ ዕድል መፍጠር ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ብለዋል። በመሆኑም ወጣቶችን በተለያዩ አደረጃጀት በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በትምህርትና ወዘተ.. በማዋቀር ለወጣቶች ሥራ መፍጠር ያስፈልጋል በማለትም ከዚህ በኃላ በውሸት ሪፖርት እየዋሹ መኖር እንደማይቻል አጠንክረው አንስተዋል። በዚህ መድረክ ላይ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድርና የስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የክልሉ የሥራ፣ የክህሎትና ኢንተርፕራዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀገረፅዮን አበበ፣ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከሲዳማ ክልል ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት የገኘነው መረጃ አመልክቷል። EBC
It's about Sidaama!