ለምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ለሠላም ቅድሚያ እንዲሰጡ የሀገር ሽማግሌዎች ጥሪ አቀረቡ
*********************
ምርጫውን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የምዕራብ አርሲ ዞን አባ ገዳ ነጌሶ ገመቹ እንዳሉት፤ ምርጫው ፍትሐዊና ሠላማዊ እንዲሆን ማድረግ የሁሉም ሰው ኃላፊነት ነው።
ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ማንነት ቢኖረንም አንድ ህዝብ ነን ያሉት አባገዳው ከብሔር ልዩነት ይልቅ በሀገር አንድነት ላይ በማተኮር ተመካክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በሶማሌ ክልል የሊበን ዞን የሀገር ሽማግሌ አሊ ሼህ ኢብራሂም በበኩላቸው፣ ፓርቲዎች ህዝብን በህዝብ ላይ ሊያነሳሱ ከሚችሉ የብሔርና ሐይማኖት አጀንዳዎች ሊቆጠቡ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የሲዳማ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት ኑሬ ኑካ፣ የዘንድሮ ምርጫ የሲዳማ ህዝብ የዘመናት ጥያቄው በተመለሰበት ወቅት የሚካሄድ በመሆኑ የተለየ ደስታ እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።
ይህን ምርጫ የተሳካ ለማድረግ ሁሉም ፓርቲዎች ሠላማዊ መንገድን መከተል እንዳለባቸው አመልክተው፤ የሀገር ሽማግሌዎችና አባቶችም ህዝቡን በመምከር የራሳቸውን ኃላፊነት እየተወጡ እንደሚገኙ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
Comments
Post a Comment