የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አሥረኛ ክልል በሆነው የሲዳማ ክልል በቀን 300 ቶን የምግብ ዘይትና ሌሎች ተዛማጅ ግብዓቶችን ማምረት የሚችል ፋብሪካ ለመገንባት፣ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልሉ ባለሥልጣናት በተገኙበት እሑድ ታኅሳስ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡ ‹‹አማ የኢንዱስትሪ ፓርክ›› የሚል ስያሜ ያለው የኢንድስትሪ ፓርኩ በአቶ አንድነት ጌታቸውና ቤተሰቦቻቸው የተቋቋመ ሲሆን፣ ድርጅቱ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ በሐዋሳ በ3,500 ካሬ ሜትር ላይ የወረቀትና የወረቀት ማሸጊያ ሲያመርት መቆየቱን፣ በተጨማሪም የምግብ ዘይት ከውጭ አገር አስመጥቶ በማከፋፈል ሥራም እንደሚታወቅ ተገልጿል፡፡ አማ የሚያስገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ በ100,000 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ በውስጡም 1.7 ቢሊዮን ብር ፈሰስ የሚደረግባቸው ሰባት ፕሮጀክቶችን እንደሚያቅፍ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡ እነዚህም የምግብ ዘይት፣ የፕላስቲክ፣ የካርቶን፣ የሳሙና፣ የጆንያ፣ የቆርቆሮና ሚስማር፣ እንዲሁም የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ በመጀመርያ የሚተከለው የዘይት ፋብሪካው ሲሆን፣ በመጀመርያው ዓመት 100 ቶን ዘይት በቀን እንዲያመርት ታቅዷል፡
It's about Sidaama!