በ2013 በሲዳማ ክልል ከ92ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጠራል፡፡
ዛሬም ቢሮው ከፌደራል የሥራ እድል ኮሚሽን ጋር በክልሉ ያለውን ስራ አጥነትን መቅረፍ በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ እየመከረ ይገኛል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ርዕሠ መስተዳዳር አቶ ደስታ ሌዳሞ የሥራ እድል ለዜጎች የመፍጠር ጉዳይ የሞት የሽረት ጉዳይ በመሆኑ ክልሉ በልዪ ትኩረት እንደሚሠራ ገልፀዋል፡፡
የወጣቱን ጉልበት ወደ ሀብት ለመቀየር በጥበብ መሥራት እንደሚያስፈልግም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ፡፡
በመድረኩ በእንግድነት የተገኙት የፌዴራል የሥራ እድል ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው አዲሱ የሲዳማ ክልል ገና ጅማሮ ላይ ሆኖ የሥራ አጥነትን ለመቅረፍ ያደረጃው አደረጃጀት ቁመና እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንደሚባለው ያማረ ነው ሲሉ አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡
እንደ ሀገር በ2013 ለ3ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ከታቀደው ውስጥ የሲዳማ ክልል 92ሺ ዘጠኝ መቶ አስራ አራት ለሚሆኑ ዜጎች ስራ እድል ለመፍጠር ያቀደውን ለማሳካት በቅንጅት እና በቁርጠኝነት ሊሠራ እንደሚገባ አቶ ንጉሡ አሳስበዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ያለውን ሠፊ መሬት አጠቃቀሙን በማዘመን እና በማልማት እና ያሉትን በርካታ ተፈጥሮአዊ ሀብቶችን ወደ ሥራ በመቀየር በክልሉ ያለውን የሥራ አጥነት ለመቅረፍ እንደሚችልም በመድረኩ በቀረበው የውይይት ፅሁፍ ተጠቁሟል፡፡
በቀረበው መነሻ ፅሁፍ ላይ የክልሉ አመራሮች ሀሳብ እና አስተያየታቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡በተለይም የሲዳማ ክልል አዲስ እንደመሆኑ ያሉትን ሀብቶች ተጠቅሞ የክልሉን ወጣቶች የሥራ እና የልማት ጥያቄን መመለስ ይችል ዘንድ የፌዴራል ሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በስፋት እየተነሳ ይገኛል፡፡
SMN 22/01/2013 ዓ.ም ሀዋሳ
Comments
Post a Comment