Skip to main content

ምክንያታዊ የሆኑ ሥጋቶችና የደቡብ ኢትዮጵያ እንቆቅልሽ

 በደስታ ሄሊሶ (ዶ/ር)

ኢትዮጵያ እንደ አገረ መንግሥት በጥልቅ ችግር ውስጥ ነች የሚለው አገላለጽ ያለችበትን ሁኔታ አሳንሶ ቢገልጸው ነው። በቅርቡ አንድ ሰው ኢትዮጵያን ‹‹ዝግ ባለ ፍጥነት በመከስከስ ላይ ያለ አውሮፕላን›› በማለት ገልጿታል። የትግራይ ክልላዊ አስተዳደር ከፌዴራል መንግሥት ጋር ኃይል ለመፈታተሽ እየተዘጋጀ በሚመስልበት፣ የኦሮሚያ ክልል በቀውስና ግራ አጋቢ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፈ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተደጋጋሚ የሆኑ ብሔር ተኮር ውጥረቶች እየተስተዋሉ ባሉበትና ከሃጫሉ ግድያ በኋላ መንግሥት የወሰዳቸው ዕርምጃዎች አገሪቱን የበለጠ በከፋፈሏት በዚህ ጊዜ የሰውየው አባባል የተጋነነ ሊሆን አይችልም።

በእነዚህ ሁሉ ክስተቶች መካከል ‹‹እናት አገር [ኢትዮጵያ]›› የሚለውን የዶ/ር ዓብይን ግጥምና ለኢትዮጵያ ያላቸውን ህልም በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ አንብቤ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚስማሙበት “እናት አገር” የሚለው ምሥል ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦችን›› የሚያመላክት ነው፣ ይህም የአንድ ቤተሰብ አካልነትን ወይም ልጅነትን የሚጠቁም ነው። ሆኖም በዚህ ዘመን በዚህ የአካልነት ወይም ልጅነት ጉዳይ ላይ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥሩ ስሜት እንደሚሰማቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም። እንዲያውም በደቡብ ያሉ ብዙዎች ይህች “እናት አገር” የሥጋ እናታችን ወይስ የእንጀራ እናታችን ናት? ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ። 

ይህ ጥያቄ በዚህ ጊዜ በተለየ ሁኔታ ለወላይታ ሕዝቦች ፋይዳ ያለው ጥያቄ ነው። በመለስ ዜናዊ የአስተዳደር ዘመን በብሔረሰቦች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ምክንያት ብዙ ወላይታዎች በሐዋሳ ተገድለዋል፡፡ እንዲሁም መተዳደሪያቸውን አጥተዋል። በኃይለ ማርያም አስተዳደር ጊዜም በኦሮሚያ ክልል ብዙ ንፁኃን የወላይታ ተወላጆች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወላይታ ብሔር በመሆናቸው ብቻ ተገድለዋል። ዶ/ር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም ብዙዎች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሲሆን፣ መተዳደሪያቸውንም አጥተዋል። በነሐሴ 2012 ዓ.ም. ጉዳዩ የበለጠ ጠነከረ፡፡ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች ስብሰባ እያደረጉ እያለ መታሰራቸውን በተመለከተ ሕዝቡ ተቃውሞ ሲያሰማ፣ የመከላከያ ሠራዊት ኃይሎች ወደ ወላይታ ተልከው ብዙ ቁጥር ያላቸውን ገድለዋል የተወሰኑትንም አቁስለዋል።  

ለእነዚህ ሁሉ ክስተቶች መነሾ የሆነው የወላይታን ሕዝብ የሚወክሉ ሰዎች ‹‹. . . ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው፤›› በሚለው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47፡2-3 ላይ በመመርኮዝ ክልል የመሆን ጥያቄ ማንሳታቸው ነው። የወላይታዎች ፍላጎት ሲዳማዎች ከነበራቸው ፍላጎት አይለይም። ክልላዊ መንግሥት ለመሆን ጥያቄ ካቀረቡት በደቡብ ከሚገኙ ከአሥር ባላነሱ አስተዳደራዊ ዞኖች ጥያቄም ጋር አንድ ነው። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ወላይታዎችን ወይም ሌሎች ሕዝቦችን በኃይል ዝም ለማሰኘት መሞከር፣ ችግሩን ያዘገየውና የበለጠ ሥር እንዲሰድ ያደርገው ይሆናል እንጂ መፍትሔ አይሰጠውም። የወላይታ ጉዳይ አሁን በመፈራረስ ላይ የሚገኘው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ፖለቲካዊ እንቆቅልሽ አካል ነው ብዬ እሞግታለሁ።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት እንቆቅልሽ ምናልባትም ሆን ተብሎ በትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (ሕወሓት) ርዕዮተ ዓለም ተፅዕኖ ሥር በነበረው፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የተቀረፀ ነው። ኢሕአዴግ 56 ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድ ላይ ከመጠፍጠፉ በፊትና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችን ከዘጠኙ ክልላዊ መንግሥታት አንዱ አድርጎ ከመፍጠሩ በፊት በደቡብ ያሉትን ሕዝቦች እንዴት ብሔርን መሠረት ባደረገ ሁኔታ ማደራጀት እንደሚቻል ስላልገባው በሐሳብ ተጠምዶ ነበር። የኤርትራ ነፃነት ያለቀለት ጉዳይ ነበር። ሁለት መቶ ሺሕ የሚጠጋ ሕዝብ ያለው ሐረሪ ክልላዊ መንግሥት እንዲሆን ታስቧል። ስድስት መቶ ሺሕ ሕዝብ ያለው ቤኒሻንጉልና 1.5 ሚሊዮን ሕዝብ ያለው አፋር ክልላዊ መንግሥት የመሆን ዕድል ሊሰጣቸው ነበር። ትግራይን፣ አማራን፣ ኦሮሞንና ሶማሌን ክልላዊ መንግሥት የማድረግ ጉዳይ ላይ ጥያቄ አልነበረም። 

ሆኖም በጊዜው ክልላዊ መንግሥታት የተመሠረቱበት መለኪያ ግልጽ አልነበረም። የሕዝብ ብዛት መለኪያ እንዳልነበረ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ሲዳማ ሦስት ሚሊዮን እንደእነ ወላይታ፣ ሐዲያና ሌሎችም እያንዳንዳቸው ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ይዘው ክልላዊ መንግሥታት መሆን በተገባቸው ነበር። 56 ብሔሮችን በአንድ ላይ አድርጎ ክልል ለመመሥረት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39፥5 ላይ የተጠቀሰው ሐሳብም መለኪያ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ይህ አንቀጽ የሚለው ሰፋ ያለ የጋራ ፀባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች፣ የጋራ ቋንቋና የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸው ሕዝቦች በአንድ ላይ ሆነው የአስተዳደር መዋቅር እንደሚመሠርቱ ሲሆን፣ ከሃምሳ ስድስቱ ብሔሮች መካከል አብዛኞቹን የሚያመሳስሏቸውና የጋራ የሚሆኑላቸው ነገሮች ትንሽ ናቸው። ምናልባት ኢሕአዴግ ገና ከመጀመርያው እነዚህን ነገሮች ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይመስለኛል አቅጣጫ ጠቋሚ የመፍትሔ ሐሳቦችን ለሚያመነጩ ቡድኖች የቤት ሥራ ሰጥቶ ነበር። ከቡድኑ አባላት አንዱም በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ነበሩ። ቡድኑም የደቡብ ሕዝቦች በአምስት የክልል አስተዳደሮች ሥር መዋቀር አለባቸው የሚል ምክረ ሐሳብ አቅርቦ ነበር። ኢሕአዴግ ምክሩን ተቀብሎ ቢሮዎችን በማደራጀት ሰዎችን መመደብ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ምክንያቱ ባልተገለጸበት ሁኔታ እነዚህን መዋቅሮች በማፍረስ ሐዋሳን ዋና ከተማ በማድረግ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ብሎ አቋቋመ። ኢሕአዴግ ለምን እንደዚህ ዓይነት የውሳኔ መንገድ ተከተለ? ለብቻውስ ለምን እንደዚህ ዓይነት ውስብስብ እንቆቅልሽ ፈጠረ? የሚሉት ጥያቄዎች በተለያዩ መንገዶች ሊብራሩ ይችላሉ። በእኔ ዕይታ ግን ኢሕአዴግ ይህንን መንገድ የመረጠው ፖለቲካዊ የበላይነትን ለማረጋገጥና ለቁጥጥር እንዲያመቸው፣ ሕዝብን የፖለቲካ መጠቀሚያ መሣሪያ ለማድረግ፣ ከፋፍሎ ለመግዛትና ሲዳማዎችን ለማረጋጋት ነው።

በመጀመርያ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥትና የተወሰኑ የአስተዳደር ዞኖች ላይ ፖለቲካዊ ጌቶች እንዲሆኑ ተሹመው ነበር። ይህ የክልሉን አጠቃላይ ፖለቲካ እንዲቆጣጠሩ አስችሏቸዋል። የክልል መንግሥቱ አመራር ከእነዚህ የፖለቲካ ጌቶች ይሁኝታ ሳያገኝ ምንም ዓይነት ቁልፍ የሆነ ውሳኔ መወሰን አይችልም ነበር። አንድ አሳዛኝ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል አንድ የደቡብ ክልል አመራር በአንድ የሕወሓት አመራር የተሰጠን ትዕዛዝ በመቃረኑ፣ በማይታመን ሁኔታ በሕወሓቱ ባለሥልጣን በጥፊ ተመትቶ ነበር። ሁሉም አመራሮች በእንደዚህ ዓይነት የውርደት ሁኔታ ውስጥ አልፈዋል ማለት አይደለም። ለህሊናቸው ያደሩት፣ ለመርሆዎቻቸው ፀንተው የቆሙትና ከፖለቲካዊ ሥልጣናቸውና ለጊዜው ከሚገኝ ቁሳዊ ጥቅም በላይ የሰውነት ክብራቸውን ያስቀደሙ ነበሩ። እነሱ ግን ተባረዋል ወይም በፈጠራ ክስ ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል። ምፀታዊ በሆነ መንገድ የፖለቲካ አጋሩን በጥፊ የመታው የሕወሓት ባለሥልጣንና ከደቡብ የሆኑት ወዳጆቹ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ተጋጭተው ነበርና በሙስና ወንጀል ተከሰው ወደ እስር ቤት ገቡ።  

ሁለተኛ የዚህ ፖለቲካዊ የበላይነትና ቁጥጥር ንድፍ የተቀረፀው የደቡብ ሕዝቦችን ፖለቲካዊ መጠቀሚያ ለማድረግ ነው። ይህም ማለት ሕወሓት/ኢሕአዴግ ደቡቦችን የተጠቀመባቸው የ“አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ግቦችን እንዲፈጸሙ መሣሪያ ለማድረግ ነበር ማለት ነው። ይህ አካሄድ ግልጽ በሆነ መንገድ የኢማኑኤል ካንትን የምግባር ቲዮሪ ይቃረናል፡፡ በዚህ ቲዮሪ መሠረት ሰዎችን ለአንድ ጉዳይ ማስፈጸሚያነት መሣሪያ አድርጎ መጠቀም የሰውነት ክብራቸውን ከመጣስ ጋር እኩል ነው። ሆኖም የሕወሓት/ኢሕአዴግ አመራሮች ጭካኔ በተሞላው መንገድ የደቡብ ሕዝቦችን በመሣሪያነት ተጠቅመውባቸዋል። በእኔ ዕይታ ለዚህ አሠራር ምቹ ሁኔታ የፈጠረው ሃይማኖት ነው።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን የፕሮቴስታንት እምነት እስከሚስፋፋ ድረስ አብዛኛዎቹ የደቡብ ሕዝቦች የባህላዊ ሃይማኖት ተከታዮች ነበሩ። ፍቅርና ሰላምን የሚሰብከውን የፕሮቴስታንት እምነት አስተምህሮ መቀበላቸው በባላንጣነትና በግጭት ውስጥ የነበሩትን የተለያዩ ብሔረሰቦች ወዳጆች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ለምሳሌ ወላይታዎች የሃድያዎች ወዳጅ፣ ከምባታዎች የሃድያዎች፣ እንዲሁም የወላይታዎችም ወዳጅ እንዲሆኑ አስችሏል። እ.ኤ.አ. ከ1937 እስከ 1941 ባለው ጊዜ ውስጥ ጥብቅ በሆነ መንገድ ሕግንና ሥርዓትን ያስተዋወቁት ወራሪ ጣሊያኖች በመጡ ጊዜ ግጭቶች እንዲቆሙ አድርገው ነበር። ቢሆንም ይህ ወዳጅነት የበለጠ እንዲጠናከር በፍጥነት በማደግ ላይ የነበረው የፕሮቴስታንት እምነት፣ ባልንጀራህንና ጠላትህን እንደ ራስህ ውደድ የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮውን ማስፋፋቱ የደቡብ ሕዝቦች እሴቶቻቸውንና ፍላጎቶቻቸውን በሰይፍ ለመጠበቅና ለማስፋፋት መሞከርን እንደ ስህተት እንዲቆጥሩ አድርጓቸዋል። ኢሕአዴግ የፕሮቴስታንት ሃይማኖትን ለፖለቲካዊ ግብ እንደ መሣሪያ አድርጎ አልተጠቀመም። ነገር ግን በቀደሙት መንግሥታት ተገቢ የሆነ አያያዝ ያልተደረገላቸውና ስደት ይደርስባቸው የነበሩ፣ አሁን ግን የሃይማኖት ነፃነትን በሚያውጀው አዲሱ ሕገ መንግሥት የተደሰቱ ፕሮቴስታንት ግለሰቦችንና ማኅበረሰቦችን መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሟል።

በአዲሱ ሕገ መንግሥት የተደነገገው የሃይማኖት ነፃነት ከመገንጠልና ራስን ከማስተዳደር፣ ቋንቋን ከማልማት፣ ባህልን ከማስፋትና ታሪክን ከመጠበቅ መብቶች ጋር ተጣምሮ ቀርቧል (አንቀጽ 39፡1-3)። ይህ ክስተት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ፍፁም እንግዳ ከመሆኑ የተነሳ በጊዜው የተፈጠረው ስሜት ወደ ቅዠት የሚጠጋጋ ደስታና ፍንደቃ ፈጥሮ ነበር። አብዛኛዎቹ የተማሩ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ዴሞክራሲያዊና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ተቀላቀሉ። ለማርክሲስት ታማኝ የሆነው አገር አቀፋዊው የኢሕአዴግ አመራር፣ የፕሮቴስታንትም ሆነ የሌሎች ሃይማኖቶችን መገለጫዎች በፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ምንም ዓይነት ሥፍራ እንዳይኖራቸው አድርጎ አዳዲሶቹ የክርስቲያን ፖለቲከኞች ግን ለርዕዮተ ዓለሙ ታማኞች እንዲሆኑ አደረጋቸው። አዳዲሶቹ የክርስቲያን ፖለቲከኞችም ፖለቲካ፣ ሴራንና ተገቢ ያልሆኑ አካሄዶችን ተማሩ። ከዚህ ቀደም ሕይወቶቻቸው የተቀረፀው በፍቅር፣ በታማኝነት፣ በትህትናና በአገልግሎት መርሆዎች ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ባይሆኑም ብዙ ሊባሉ የሚችሉ ለእነዚህ መርሆዎች ለመቆም ወይም ታማኝ ለመሆን ተቸገሩ። እንዲያውም የተወሰኑት ራስ ወዳድ፣ ታማኝነት የጎደላቸው፣ ዕብሪተኛና በጥላቻ የተሞሉ ሆኑ። በፖለቲካ ያገኙትን ሥልጣን ማኅበረሰብን ለማሻሻል የሚጠቀሙት መንገድ መሆኑ ቀርቶ፣ በራሱ ግብ እንደሆነ አድርገው ወሰዱ። የፖለቲካ ሥልጣንም ለራስ ጥቅም ማካበቻ መንገድ ሆነ። ህልውናቸው የተመሠረተው ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ እሴቶች ባላቸው ያልተበረዘ ታማኝነትና ለበላይ ጠባቂዎቻቸው ባላቸው ሙሉ መታዘዝ እንደሆነ እንዲያምኑ ተደረገ።   

ሦስተኛ ኢሕአዴግ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚኖረውን ሕዝብ የፖለቲካ መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀም መሠረት የሆኑለት፣ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› እና “ከፋፍለህ ግዛ” የሚል ዓይነት አስተሳሰብ የያዘ የማኪያቬሊ መርህ ነው። ማኪያቬሊ “ዘ ፕሪንስ” በሚለው ሥራው እንደገለጸው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የበላይ ጠባቂዎች፣ ደቡብን በፖለቲካ የበላይነት ለመቆጣጠርና ሕዝቡን እንደ መሣሪያነት ለመጠቀም በሰውና በእንስሳ ዓለም የሚገኙ ሕጎችንና ኃይልን ተጠቅመዋል። ማኪያቬሊ የጣሊያን ልዑላን ወይም ገዥዎች ሰዎችን በእንስሳ በማስመሰል በአንበሳና በቀበሮ መልክ አሠልፈው እንዲያቸው መክሯቸዋል። አንበሳ ኃይለኛ ነው ግን ራሱን ከወጥመድ መከላከል አይችልም፣ ቀበሮ ደግሞ ከተኩላ ራሱን መከላከል አይችልም። ቀበሮ ወጥመድን አስቀድሞ ያያል፣ አንበሳ ደግሞ ተኩላዎችን ያስፈራራል። ነገር ግን ሁሉም ወዳጆች ሳይሆኑ አንዳቸው ለሌላቸው ጠላቶች ናቸው። በማኪቬሊያዊ አስተሳሰብ ኢሕአዴግ አንበሳዎችንና ቀበሮዎችን በመፍጠር፣ እርስ በርሳቸው ጠላቶች የሆኑ ነገር ግን እያንዳንዳቸው የየራሳቸውን የግል ፍላጎቶች ለማስከበር አንዳቸው ሌላቸውን የሚጠብቁ እንዲሆኑ ማድረግን ፖለቲካዊ ጥበብ እንደሆነ አድርጎ አመነ። አንበሶችና ቀበሮዎች እርስ በርስ ይጠባበቃሉ፣ ነገር ግን በመካከላቸው ፍቅር ወይም የእርስ በርስ መተማመን የለም። ለማኪያቬሊ ሰዎች ውስብስብ ያልሆኑ፣ እንዲሁም ለዛሬ ፍላጎቶቻቸውና ለግል ጥቅሞቻቸው ተዥዎች የሆኑ ፍጥረታት ናቸው። ስለዚህ ባለሥልጣናት ይህን የሰው ባህሪ ተረድተው የበታቾቻቸው አንዳቸው ሌላቸውን መጠበቃቸው ብቻ የሥልጣናቸውን ስኬታማነት እንደማያረጋግጥ መረዳት አለባቸው። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ቀበሮዎችን ከተኩላ ይጠብቁ የነበሩ አንበሶች ወጥመድ ውስጥ ሲገቡ እያዩ ዝም ማለት ይኖርባቸዋል። አንበሶች ደግሞ አንዳንዴ ጠባቂዎቻቸው የነበሩትን ቀበሮዎች በጭካኔ መግደል አለባቸው። ይህ በደቡብ አካባቢ በግልጽ የሚታይ እውነታ ነበረ።

በየጊዜው በሚደረጉ ግምገማዎች ኢሕአዴግ የደቡብ ፖለቲከኞች ለግልና ለፖለቲካዊ ትርፎች እንዲጠፋፉ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ነበር። ከታማኝነትና ከቅንነት ይልቅ ሰዎችን በብልጠት በተሞሉ ሴራዎች ግራ ማጋባት የላቁ ነገሮችን መፈጸም እንደሚያስችላቸውና ትልቅ ቦታ እንደሚያደርሳቸው እንዲያምኑ አደረጋቸው። በማኪቬሊያን ትምህርት መሠረት ሥልጣን ላይ እንዲወጡ እስከ ረዳቸው ድረስ ከእውነት፣ ከልግስና፣ ከሰብዓዊነት፣ ከሃይማኖት ከሌሎችም በጎ እሴቶች ተቃራኒ መንገድ መሄድን ብዙ ፖለቲከኞች መረጡ። ፖለቲካ ለኃይልና ለሀብት የሚደረግ መራር ትግልና ውድድር ተደርጎ ተሳለ። በዚህ ዜሮ ድምር በሆነ ጨዋታ ውስጥ ዝምድናና ሌሎችን መርዳት ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ወንድም በወንድሙ ላይ ፊቱን እንዲያዞርና አንዱ አንዱን ጥሎ ተረማምዶበት እንዲያልፍ አድርጓል። በመታመንና በታማኝነት ላይ የተመሠረተው ማኅበራዊ ሀብት እንዲቃለል ተደርጓል። አለመተማመንና አለመረጋጋት በየአካባቢው ነገሠ። የፖለቲካ ጮሌዎች ይህን ሁሉ ለራሳቸው ጥቅም ከማዋላቸው በተጨማሪ፣ የፖለቲካ ግባቸውን ያለምንም እንቅፋት እንዲፈጽሙ አስችሏቸዋል። የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የክፋት ፖለቲካን ለሚያራምዱ የድግስ ሥፍራ ሆነላቸው።

በመጨረሻም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግሥት የተፈጠረው ለፖለቲካዊ ቁጥጥርና መሣሪያነት፣ እንዲሁም የማኪቬሊን ዓይነት አስተሳሰብ ተግባራዊ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ሲዳማዎችንም ለማርካት ጭምር ነው። ሲዳማዎች በአቶ ወልደ አማኑኤል ዱባለና በሲዳማ ነፃነት ግንባር በመመራት ከ1970ዎቹ ጀምሮ ወታደራዊውን የደርግ አገዛዝ ተዋግተዋል። ጠንካራ የሆነውን የኢትዮጵያ ወታደራዊ ኃይል ማሸነፍ ሲያቅታቸው አቶ ወልደ አማኑኤል አገሪቱን ለቀው ተሰደዱ። በሱዳን ቆይታቸው ከአቶ መለስ ዜናዊና ከሌሎችም ጋር የመተዋወቅ ዕድል አግኝተዋል። እ.ኤ.አ. በ1991 ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ አቶ ወልደ አማኑኤልና ፓርቲያቸው የአዲስ አበባው የሽግግር ምክር ቤት አካል እንዲሆኑ ተጋብዘው መጡ። በመለስ ዜናዊ የሚመራው የሽግግር ምክር ቤት ከተመሠረተ በኋላ፣ ሲዳማዎች የራሳቸውን ክልላዊ ምክር ቤት የመመሥረት ፍላጎታቸው እያደገ መጣ። በዚህ ምክንያት አቶ ወልደ አማኑኤል በመለስ ዘንድ ያላቸው ወዳጅነት ቀነሰ። በሲዳማ ከተደረገባቸው የግድያ ሙከራ በኋላ አቶ ወልደ አማኑኤል አገር ለቀው ተሰደዱ፣ ከጊዜ በኋላ ግን ተመልሰዋል።

ይህ እየሆነ ሳለ ኢሕአዴግ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥትን ሐዋሳን ዋና ከተማው በማድረግ መሠረተ። የሲዳማ ተወላጅ የሆነን ሰው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አድርጎ ሾመ። ይህ ግን የሲዳማዎችን ሕገ መንግሥታዊ የሆነ ራስን የማስተዳደር ፍላጎት አላቀዘቀዘውም። ይህ ስሜት በኋላ ላይ ከወላይታ ብሔር የሆኑት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሆነው በተሾሙ ጊዜ የበለጠ አደገ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከሲዳማ ውጪ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሆኖ የተሾመ የለም። ኢሕአዴግ ይህንና ሌሎች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘዴዎችን ቢጠቀምም የሲዳማዎችን ክልል የመሆን ጥማት ሊያረካ አልቻለም። ፖለቲካዊ ጭቆናና ኃይል መጠቀምም እንደ አማራጭ ቢወሰድም ቅሬታው ቀጥሏል። ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር በሆኑ ጊዜ ሲዳማዎች አዲስ የተገኘውን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት በመጠቀም ክልላዊ መንግሥት የመሆን ፍላጎታቸውን እ.ኤ.አ. በታኅሳስ 2020 ላይ ሊያሳኩት በቅተዋል። ነገር ግን ይህ ክስተት የደቡብን ፖለቲካዊ እንቆቅልሽ የበለጠ አወሳስቦታል። 

የወላይታም ጥያቄ የዚህ እንቆቅልሽ አካል ነው። በዚህ ጊዜ እንቆቅልሹን ይበልጥ ያወሳሰበው የፌዴራል መንግሥት የደቡብ ክልላዊ መንግሥትንና የደቡብ ሕዝቦችን መፃኢ ሁኔታ የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ በግልጽ ሳያስቀምጥና በፍኖተ ካርታውም ላይ ስምምነት ላይ ሳይደረስ፣ የሲዳማ ጥያቄን የመለሰበት መንገድ እንደሆነ ብዙዎች ይተቻሉ። ትችቱ መሠረተ ቢስ አይደለም። ይሁን እንጂ በጊዜው የነበሩ ዕይታዎቻችንና ተስፋዎቻችን ምንም ቢሆኑ የመንግሥትን ድክመቶች ለማሳየት ብቻ መሞከር፣ አሁን በውጥረትና በፈተና ለተሞላች ደግሞም ነገዋ የጨለመ ለሚመስል አገራችን የሚያበረክተው ፋይዳ የለም። ዋና ጥያቄያችን መሆን ያለበት የደቡብን እንቆቅልሽ ለመፍታት መንግሥት አሁን ምን ማድረግ አለበት የሚል ነው። በእኔ ሐሳብ አሁንም መንግሥት የደቡብን እንቆቅልሽ ለመፍታት በሚያደርገው ሒደት በትዕቢት፣ በማናለብኝነት፣ በግድየለሽነት፣ አውቅላችኋለሁ በማለትና በብልጣ ብልጥነት ውሳኔዎችን የሚሰጥ ከሆነ ኢትዮጵያ እንደ አገር አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ትገባለች። ስለዚህ በትህትና የሚከተሉትን ምክረ ሐሳቦች አቀርባለሁ።

በመጀመርያ መንግሥት በአጠቃላይ የአገሪቱን ሕግና ሥርዓት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም የወላይታ የሕዝብ መሪዎችን፣ ፖለቲካዊ አንቂዎችን፣ ሃይማኖታዊ መሪዎችንና ተራ ሰዎችን ማሸማቀቅ፣ መግደልና ማሰር በፍርድ ቤትም ማንገላታት ማቆም አለበት። እንደሰማሁት ከሆነ የወላይታ አመራሮች ከደቡብ ክልላዊ መንግሥት አገዛዝ ለመውጣት በተናጠል ዕርምጃ ወስደዋል። ይህ አካሄድ ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ስህተት ራሱ በውይይትና በንግግር ሊፈታ ይችል ነበር። የወላይታ ጥያቄ የሌሎችም አስተዳደር ዞኖች ጥያቄ ነው። ስለዚህ መንግሥት ክልል እንሁን ለሚለው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለሚመጣ ጥያቄ አመፅ የሚያነሳሱ ምላሾችን ሳይሆን፣ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መፍትሔ ሊፈልግ ይገባዋል።   

ሁለተኛ የፌዴራል መንግሥት የደቡብ ሕዝቦችን ሁኔታና ስሜት፣ በብዙ ርህራሔና ራሱን በእነሱ ጫማ ሥር አድርጎ ሊረዳ መሞከር አለበት። ለአብዛኞቹ የደቡብ ሕዝቦች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የተባለው የኤደን ገነት አልነበረም። ከሐዋሳ ርቀው የሚኖሩ ብዙዎች (ለምሳሌ እንደ ጂንካና ቤንች ማጂ) በኢፍትሐዊነትና በእኩል ዓይነት ባለመታየት ተንገላተዋል። ሲዳማ ያልሆኑ ብዙ የሐዋሳ ነዋሪዎች የመገለልና የመድልኦ ስሜት እንደሚሰማቸው ይናገራሉ። ለአስተዳደር ዞኖችና ወረዳዎች የተመደቡ በጀቶች፣ እንዲሁም የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎች የራሳቸውን ጥቅም በሚያሳድዱ በሐዋሳ በከተሙ የመንግሥት ሠራተኞችና ሙሰኛ የፖለቲካ ባለሥልጣናት ለግል ጥቅም ውለዋል። በአጭሩ የደቡብ ሕዝቦች በደንብ ባልታሰበበትና ፍትሐዊ ባልሆነው የኢሕአዴግ የፖለቲካ ቀመርና መዋቅራዊ ድልድል ምክንያት በብዙ በኩል ተጠቂ ሆነዋል። የደቡብ ሕዝቦች የደረሰባቸው ኢፍትሐዊነትና ሚዛናዊ ያልሆነ ሁኔታ በድጋሚ ሊጤን ይገባዋል፡፡ እንዲሁም የሕዝቡን ስሜትና ፍላጎት ባገናዘበ መንገድ ፖለቲካዊ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል።

ሦስተኛው የፌዴራል መንግሥት ሁሉንም ድምፆች በእኩል መስማት አለበት። ይህ የመስማት ሒደት መጀመር ያለበት መንግሥት የደቡብ ሕዝቦችን እንቆቅልሽ ለመፍታት በሄደበት መንገድ ላይ ስህተቶች እንደነበሩ በመቀበል ሊሆን ይገባዋል። አንዳንዶች እንደሚያምኑት እስካሁን የተደረጉ ሙከራዎችና የተጠቆሙ መፍትሔዎች እውነተኛ አይደሉም። እውነተኛ ይሁኑም አይሁኑም በ2011 ዓ.ም. የሳይንሳዊ ጥናት ውጤት ነው ተብሎ ሲዳማ ክልል ከሆነ በኋላ ሃምሳ አምስቱንም ሕዝቦች በአንድ ክልላዊ መንግሥት ሥር ለማስቀጠል የቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት አላገኘም። እንዲሁም ቀጥሎ በ2012 ዓ.ም. በ’ሰላም አምባሳደሮች’ የተጠና ጥናት ነው ተብሎ በተለያዩ ክልላዊ ክላስተሮች ለመከፋፈል የተደረገው ሙከራ ተቀባይነት እያገኘ አይደለም። በእነዚህ ሁሉ ሙከራዎች ውስጥ መንግሥት ብዝኃ ድምፆችን ከመስማት ይልቅ የተመረጡ ድምፆችን እየሰማ ነው የሚል ስሜት አለኝ። ይህ አካሄድ አሁን መቀየር አለበት።  

አራተኛ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ኢሕአዴግ እንዳደረገው ለራሱ የሚመቸውን ፖለቲካዊ መስመር አበጅቶ፣ ያን መስመር ላለማስነካትና ፖለቲካዊ የበላይነቱን ለማስጠበቅ በደቡብ ሕዝቦች ላይ ሕዝቡ የማይፈልገውን መዋቅራዊ አሠራር መዘርጋት የለበትም። ይህ መንግሥት እንደ ኢሕአዴግ መንግሥት ሕዝቡን እሱ ለሚፈልገው ዓላማና ግብ መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀምና ከፋፍሎ ለመግዛትም መሞከር የለበትም። በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ ለመፈለግ በሚደረግ ፖለቲካዊ ሒደት ውስጥ የደቡብ ሕዝቦችን ወደ ጎን ሊያደርጋቸው አይገባም። የደቡብ ሕዝቦች ችግር የኢትዮጵያም ችግር ነው፣ የኢትዮጵያ ችግር እንዲሁ የደቡብ ሕዝቦች ችግር ነው። ኦሮሞዎችና አማሮች ወንድማማቾች ናቸው ስለዚህ የሁለቱ ኅብረት የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ዋናው መንገድ ነው የሚል የማያቋርጥ ንግግር እሰማለሁ። በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለ ፍቅርና ኅብረት ለኢትዮጵያ መልካም ነገር መሆኑ ላይ ምንም ጥርጥር የለኝም። ሆኖም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ‹‹የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው ዘር ምንጭ›› በተባለው መጽሐፋቸውና በሌሎችም መድረኮች ኦሮሞና አማራ የጋራ የዘር ግንድ አላቸው፣ ስለዚህ የእነሱ ኅብረት ወሳኝ ነው እያሉ የሚያራምዱት ዓይነት ጤናማ ያልሆነ አቋም እንደ ደቡብ ሕዝቦች ያሉትንና ሌሎችንም ብሔሮች የሚያገል ነው። ‘ኦር ወይም አማራ’ በሚል መጠሪያ ስም ሥር የሚደረገው እንቅስቃሴና በጠቅላላውም አንድን ብሔር ወይም የተወሰኑ ብሔሮችን ያማከሉ ግቦችን ለማሳካት ተብሎ፣ ጤናማ ያልሆነ ፖለቲካዊ ትብብር ወይም ወዳጅነት መፍጠር የኢትዮጵያ መፃኢ ሁኔታን አደጋ ውስጥ ይከተዋል ብዬ አምናለሁ። በሌላ ሥፍራ ለመሞገት እንደ ሞከርኩት ለመፍትሔዎቹ የሚደረጉ የትኞቹም ጥረቶች ኢትዮጵያ አንድ የእህትማማቾችና የወንድማማቾች አገር ነች በሚል አቋም ላይ መመሥረት አለባቸው ብዬም አምናለሁ (https://hintset.org/articles/view-point/one-nation-of-sisters-and-brothers)።

በመጨረሻም ከዞኖች በኩል የሚመጡ ክልላዊ መንግሥት የመሆን ጥያቄዎች/መሻቶች ሕገ መንግሥታዊ ቢሆኑም በደቡብ ውስጥ 55 ክልላዊ መንግሥታትን ማቋቋም መቻሉ በጣም አጠራጣሪ ነው። አሁን ያሉትንም የዞኖች አወቃቀር ተከትሎ ክልሎችን ማቋቋምም እጅግ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ለዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍትሔ በማምጣት ሒደት ውስጥ በተናጠል የሚደረጉ አካሄዶች ሊወገዱ ይገባል። አንዳንዶች ለመቀበል ቢቸገሩም ክልላዊ መንግሥት የመሆን መሻቶችና መዘዞቻቸው የሕገ መንግሥቱ ጉድለቶች መፍትሔ ሳይሰጥባቸው የሚቀረፉ አይደሉም። ሕገ መንግሥታችን ብዙ ጥንካሬዎች ያሉት ቢሆንም እንደ አለመታደል ሁኖ ከአንዱ ሕዝብ ይልቅ ለሌላው፣ ከአናሳው ይልቅ ለብዝኃው የሚያዳላ ነው። እነዚህ ጉድለቶች በግልጽና በታማኝነት መፍትሔ ካልተሰጣቸው የደቡብ እንቆቅልሽ ይቀጥላል እንጂ አይቆምም። በውጤቱም ቅሬታው እያደገ ስለሚመጣ የሚጠበቀውን ብሔራዊ አንድነት፣ ሰላምና ብልፅግናን ማምጣት አይቻልም የሚልም ፍርኃት አለኝ። ስለዚህም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት በጊዜ ገደብና በዕቅድ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎችም የኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ በቁጥር አናሳ የሆኑ ብሔሮች ሕገ መንግሥታዊውና ነባራዊው ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ እውነተኛ የሆነ አገራዊ ስምምነትን እንዲፈልግ እያልኩ እማፀናለሁ። ይህ ዝግ ባለ ፍጥነት ለመከስከስ እየወረደ ያለን አውሮፕላን የምትመስለው ኢትዮጵያ ከመከስከስ እንድትተርፍ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው destah@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ 

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

የለበሰው ያደፈ ቁምጣና ሹራብ ከቅዝቃዜው አላዳነውም፡፡ ካፊያው ልብሱን አርሶታል፡፡ ሽው እያለ ከሐይቁ የሚነሳው ነፋስ የሚፈጥረው ቅዝቃዜ ያንቀጠቅጠዋል፡፡ የተጫማው ያረጀ ሲሊፐር እግሩን ከምንም አላዳነውም፡፡ በባዶ እግሩ የሚራመድ ያህል ጨቅይቷል፡፡ ተደባዳቢ ይመስል ፊቱ የተሞነጫጨረ ነው፡፡ ገና 12 ዓመቱ ቢሆንም፣ ቁመናው እንደ ትልቅ ሰው ግዙፍ ነው፡፡ የሚለብሰውን እንደ ልቡ ባያገኝም፣ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ቤሳቢስቲን የሌላቸው ወላጆቹን አያስቸግርም፡፡ ከቤተሰቦቹ ጋር ከሚኖሩበት ታቦር ተራራ ጀርባ ወዳለው ሐዋሳ ሐይቅ ከወረደ እንኳንስ የራሱን የቤተሰቦቹንም የዕለት ጉርስ የሚሸፍንበት ገንዘብ አያጣም፡፡ የአስጎብኚነት ዕውቀት፣ ከሐይቁም ውስጥ ዓሳ የሚያጠምድበት መረብም ሆነ ፈቃድ የለውም፡፡ ሙሉቀን (ስሙ ተቀይሯል) እና ጓደኞቹ ሐይቁን ለመጎብኘት የሚሄዱ ጎብኚዎች በካሜራቸው ጥሩ ፎቶ እንዲያስቀሩ ድባቡን የማሳመር ሥራ ይሠራሉ፡፡ ካሜራውን ይዞ ቁጭ ብድግ እያለ ጥሩ ፎቶ ለማንሳት ጥረት የሚያደርግ ሲያዩ፣ ቆርጠው የያዙትን የዓሳ ሥጋ ይዘው ጠጋ ጠጋ ይላሉ፡፡ ቁርጥራጩን የዓሳ ሥጋ ምግብ ለሚቀሙት አባኮዳዎች ሻሞ ይላሉ፡፡ የተወረወረላቸውን ቀድመው ለመቅለብ አባኮዳዎቹ ክንፋቸውን እየመቱ ወደ ላይ ብድግ ይላሉ፡፡ የናሽናል ጆግሪፊ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ያነሱት ዓይነት ፎቶዎች ሳያስቡት ያነሳሉ፡፡ በሁኔታው ተደስተው ደጋግመው ድንቅ ፎቶዎችን ለመውሰድ ሲዘጋጁ እነ ሙሉቀንም አጀንዳቸውን ይፋ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ አቶ ዳዊት አብርሃም ‹‹አንዱን ዓሳ በአሥር ብር ገዝቼ ነው እንዲህ የማዘጋጀው፤›› በማለት በቅድሚያ  መረጃ ይሰጣሉ፡፡ ለቀጣዩ ዜና በዚህ መልኩ እንዲዘጋጁ ካደረጉ በኋላ፣ ሌሎች ሰዎች መቶም ሁለት መቶም ብር እንደሚሰጧቸው ቀለል

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የመንግሥት ስልጠና የምርጫ ቅስቀሳ አካል ነው ብሏል  የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ለምን ወጣ መባሉ ተገቢ አይደለም - ምርጫ ቦርድ ምርጫ ቦርድ ከኢህአዴግ ተፅዕኖ ሙሉ ለሙሉ ነፃ መሆኑ ሳይረጋገጥና የምርጫ አፈፃፀም ችግሮች ሳይወገዱ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ለማወጅ መዘጋጀቱ ተገቢ አይደለም ሲል ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመሩት ኢማዴ-ደህአፓ ተቃወመ፡፡ መንግስት፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎችን ጨምሮ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየሰጠ ያለው ስልጠና የምርጫ ቅስቀሳ አካል ነው ሲልም ፓርቲው ኮንኗል፡፡  የኢትዮጵያ ማህበረ ዴሞክራሲ ደቡብ ህዝቦች አንድነት ፓርቲ ሰሞኑን ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባስገባው ግልፅ ደብዳቤ፤ ያለፉት አገር አቀፍና የአካባቢ ምርጫዎች ከመካሄዳቸው በፊት በምርጫ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር የሚወያይበት መድረክ እንዲዘጋጅ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም እስካሁን ከቦርዱ የተሰጠ ተግባራዊ ምላሽ የለም ብሏል፡፡  ሃገሪቱ “በአንድ አውራ ፓርቲ” ብቸኛ ቁጥጥር ስር መውደቋ አደገኛና አሳሳቢ ነው ያለው ፓርቲው፤ የመድብለ ፓርቲ ስርአት የመገንባት ተስፋችን ጨርሶ እንዳይከስም ቦርዱ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የሚካሄድበትን ሁኔታ ለመፍጠር ገዥው ፓርቲና ሃቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚወያዩበት መድረክ እንዲያመቻች በህግ ስልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድ የገባውን ቃል በማጠፍ መድረኩን ሳያመቻች የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀቱ ፋይዳ የለውም ብሏል - ፓርቲው፡፡  ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በተሻሻለው የምርጫ ህግ፣ ለቦርዱ የተሰጠውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ የማስተባበር ስልጣን ለመቀማት ታማኝ ፓርቲዎችን በተቃዋሚ ስም አሰባስቦ “የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ” በመፍጠር የምርጫ ውድድር አሯሯጭ አሰልፏል ሲ

29 ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ የጫነ አንድ ተሸከርካሪ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ገልፀ

29 ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ የጫነ አንድ ተሸከርካሪ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ገልፀ፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ ኮለኔል ሮዳሞ ኪአ እንዲሁም ኮማንደር ኢዮብ አቤቶ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መሰረት ትላንት ምሽት 5፡00 አካባቢ ኮድ 3/ 34480 አ.አ ታርጋ ቁጥር በለጠፈ አይሱዙ ኤፍ.ኤስ.አር ተሸከርካሪ 29 ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በመኪናው ከፋብሪካ ውጭ በተሰራ በቀላሉ የማይገኝ ሚስጥራዊ ቦታ ተደብቆ ሲጓዝ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፀዋል፡፡ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያውን ሲያጓጉዙ የነበሩት የመኪናው አሽከርካሪ፣ የህገ-ወጥ ጦር መሳሪያው ባለቤት እና የመኪናው እረዳት በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተገልጿል፡፡ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መረጃው ከሳምንት በፊት አስቀድሞ በደረሰ ጥቆማ የታወቀ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ብቃት ያለቸውን የፖሊስ አመራሮች በመመደብ ጉዳዩ በሚስጥር ሲጣራ ቆይቶ ትላንት ምሽት በቁጥጥር ስር መዋሉ ነው የተገለፀው፡፡ የጦር መሳሪያው ከየት ተነስቶ ወደየት እንደሚሄድ ለምን ዓላማ ሊውል እንደተፈለገ ጭምር መረጃዎች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን ጉዳዩ በምርመራ ሂደት ላይ በመሆኑ ሳይገለፅ ቀርቷል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ የፀጥታ ሀይሉን አቅም በማጠናከር እና ከህዝብ ጋር በመቀናጀት ማንኛውንም አይነት ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ሮዳሞ ኪአ ገልፀዋል፡፡ በዚህም የከተማዋ ሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እና እየተጠናከረ መምጣቱን ኮለኔል ሮዳሞ ገልፀው