በሲዳማ ክልል በአምራች ዘርፍ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት የ10 አመት እቅድ ወጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
የክልሉ የስራ እድል ፈጠራ ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ በዘርፉ መልካም እድሎችና ተግዳሮቶች ዙሪያ የሚመክር ጉባኤ በሀዋሳ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ ቡላዶ በቀጣዮቹ አመታት የክልሉ ወጣቶችን የስራ እድል የሚያሰፉ ስራዎችን ለመስራት በጥናት ተለይቶ ርብርብ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለክልሉ ሁለንተናዊ ብልጽግና እና ልማት እውን መሆን አስተማማኝና ሰፊ መሰረት ያለው ተወዳዳሪ የአነስተኛና መካከለኛ የማንፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት የነበሩ ማነቆዎች ተለይተው የመፍትሄ ርምጃዎች ለመውሰድ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነውም ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር የሚያግዙ አስቻይ ሁኔታዎች ያሉት ቢሆንም፤ በዘርፉ በቂ ስራ ባለመሰራቱ በርካታ ስራአጥ ወጣቶች እንደሚገኙም በመድረኩ ተጠቁሟል።
በክልሉ የነባር ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት አሁን ካለው ከ50 በመቶ አፈጻጸም በቀጣዮቹ 10 አመታት ጊዜ ውስጥ 85 በመቶ ለማድረስ መታቀዱም ተገልጿል።
የአምራች ዘርፉ የ6.8 በመቶ የኢኮኖሚ ድርሻም ቢሆን በ2022 ዓ.ም 17 በመቶ ለማድረስ ይሰራልም ነው የተባለው።
የክልሉ ስራ እድል ፈጠራ ኢንደስትሪና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ በቀጣዮቹ 10 አመታት በተለይ በአምራች ዘርፍ ከውጭ የሚገቡ ገቢ ምርቶችን የሚተኩ ኢንዱስትሪዎች በክልሉ ተስፋፍተው በኢኮኖሚው ውስጥ አሁን ካለው የ30 በመቶ አበርክቶ እስከ 60 በመቶ እንዲደርስ በቀርጠኝነት ይሰራልም ተብሏል።
በመድረኩ የተገኙት የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ኤልያስ በበኩላቸው፣ በክልሉ ከዚህ ቀደም የነበረው የአደረጃጀት ችግር ተቀርፎ ወደ ስራ በመገባቱ አንገብጋቢ የሆነው የወጣቱ የስራ እድል ችግርን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቢሮው የዘርፉን የእስካሁን አፈጻጸም ችግሮች፣ መልካም እድሎች እና አስቻይ ሁኔታዎችን በሚቀርቡ ጥናቶች ላይ ተመርኩዞ የሀዋሳና የይርጋለም አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ ከወረዳና ከክልል ከተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በሀዋሳ ከተማ እየገመገመ ይገኛል።
©FANABC
Comments
Post a Comment