በኢትዮጵያ ስምንት የመንግሰት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል በመባል መለየታቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ጥራት ዙሪያ ያካሄደውን የምርምር ግኝቶች ላይ ትላንት ከባለድርሻዎች ጋር ተወያይቷል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ወርቁ ነጋሽ በወቅቱ እንደገለጹት በሃገሪቱ የሚገኙ 46 ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በአጠቃላይ ትምህርት በሚል በሶስት ደረጃዎች ተለይተዋል፡፡
ባለፉት አመታት በርካታ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን ሲያበረክቱ የቆዩና ወደፊትም አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል የተባሉ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ዘርፍ የልህቀት ማእከል እንዲሆኑ መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡
“ጎንደር፣ አዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ መቀሌ፣ ጅማ፣ ሃዋሳ፣ አርባምንጭና ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማእከል እንዲሆኑ ተለይተዋል” ብለዋል።
ለአንድ ሀገር ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ችግር ፈቺ ምርምር ቁልፍ ሚና እንዳለው የገለጹት ዶክተር ወርቁ “ያደጉ ሃገሮች የእድገት ሚስጥርም ከዚህ የመነጨ ነው” ብለዋል፡፡
የምርምር ዩኒቨርሲቲዎቹ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አቻ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አቅማቸውን ለመገንባት በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡
ሌሎች 15 የመንግሰት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ መለየታቸውን ተናግረዋል ።
ዩኒቨርሲቲዎቹ በቂ እውቀትና ክህሎት ያዳበረ ዜጋ ማፍራት እንዲችሉ ተከታታይ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል።
ቀሪዎቹ 23 ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ አጠቃላይ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ የተለዩ መሆኑን ዶክተር ወርቁ አስታውቀዋል ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ላለፉት ሶስት አመታት ጎንደር ከተማን ጨምሮ በሰሜን፣ በማእከላዊና በምእራብ ጎንደር ዞኖች በተመረጡ 1 ሺህ 343 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በትምህርት ጥራት ዙሪያ ጥናትና ምርምር መካሄዱን ገልጸዋል፡፡
በምርምር ውጤቶቹ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ምክክር እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል ።
“በዩኒቨርሲቲው የስነ ትምህርት ኮሌጅ መምህራን የተዘጋጀው የምርምር ውጤት ለፖሊሲ አውጪዎች ጠቃሚ ግብአት ሆኖ የሚያገለግል ነው” ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ናቸው፡፡
ባለፈው አመት ዩኒቨርሲቲው ከ200 በላይ የምርምር ስራዎችን ማካሄዱን አስታውሰዋል ።
ዘንድሮም በተለያዩ ዘርፎች ምርምር ለማካሄድ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እያካሄደ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ ማሳወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።
ለአንድ ቀን በተካሄደው ውይይት የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከጎንደር ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ መምህራንና የትምህርት አመራሮች ተሳትፈዋል ።
©ebc
Comments
Post a Comment