ሀዋሳ ጥቅምት 1/2013 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል ከ156 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለፁ።
አቶ ደስታ ይህን የገለፁት እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት 5ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ዋና ዋና የ2013 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ ነው ።
እንደ ርዕሰ መስተዳደሩ ገለፃ ሲዳማ ክልል ሆኖ ከተቋቋመ በኋላ የአደረጃጀት መዋቅሩን በሰው ኃይል የማጠናከር ሥራ እንዲሁም የክልሉን ፀጥታና ሠላም አስጠብቆ የማስቀጠል ሰፊ ተግባር ሲከናወን ቆይቷል።
የኮሮና ወረርሽኝ የከፋ ተጽዕኖ ሳያሳድር የክልሉን የልማትና ሌሎች ሥራዎች ለማስቀጠልም ሰፊ ርብርብ መደረጉንም ተናግረዋል።
በቀጣይ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከየአካባቢው ህዝብ ጋር ሲደረግ የቆየው ውይይትም ውጤታማ እንደነበርና በ2013 በትኩረት ከሚከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል የሥራ ዕድል ፈጠራ አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በክልሉ በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ደስታ ይሁን እንጂ እነዚህ ወጣቶች ሰርተው የሚለወጡበት በቂ ኢንቨስትመንት ማስፋፋትና በቂ ሀብት ማፍራት ባለመቻሉ ላለው የሰው ኃይል ሥራ መፍጠር እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡
ይህን ችግር ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የክልሉን ሠላም በማስጠበቅ ኢንቨስተሮችን በስፋት መሳብና የሥራ ዕድልን ማስፋፋት በበጀት ዓመቱ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ለ103 ሺህ 920 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንዲሁም ለ52 ሺህ 149 ዜጎች ጊዜዊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰራና ዋናው ትኩረት ለሴቶችና ወጣቶች መሆኑን ባቀረቡት ዕቅድ ጠቁመዋል።
ለዚህ የስራ ዕድል ፈጠራ ከቁጠባ፣ ከዕዳ ማስመለስ እንዲሁም ከመንግስት ድጋፍ ከ798 ሚሊዮን ብር በላይ ለብድር የሚሆን ገንዘብ ለማቅረብ በርብርብ ይሰራልም ብለዋል፡፡
ግብርናን በማዘመንና በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ የኤክስፖርት ምርቶችን በሥፋትና በጥራት ማምረት፣ የህዝቡን የመሰረተ ልማት ጥቄዎች ደረጃ በደረጃ መፍታት፣ ሠላምና ፀጥታን ማስጠበቅ እና ሌሎች ጉዳዮችም የበጀት ዓመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡
Comments
Post a Comment