በሲዳማ ክልል የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ የሚመለስ አደረጃጀት እየተዘረጋ ነው-ርእሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ
***************************************
በሲዳማ ክልል የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል አደረጃጀት እየተዘረጋ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።
ርእሰ መስተዳድሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት አደረጃጀቱ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የአዳዲስ ዞኖች መዋቅርና ነባር ወረዳዎችን መልሶ የሚያጠናከር ሥራ ነው።
ከዚህ በተጓዳኝም ክልሉ የሚመራበት ስትራቴጂ እና ዓመታዊ እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይ የክልሉ አደረጃጀት በዋናነት የኅብረተሰቡን ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ እና ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን በሚያስችል መልኩ የሚዘረጋ መሆኑን አስታውቀዋል።
"አዲስ መዋቅር ለመዘርጋት ጥናት ተካሂዷል" ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ በዚህ ረገድ ዋና አካሄድ የሚገኘውን ሀብት በቁጠባ በመጠቀም ውጤት ለማስመዝገብ እና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት ማመቻቸት መሆኑን ገልጸዋል።
ያካሄዱት ጥናት ይህንን የሚደግፍ መሆኑን አመልክተው፣ በዚህም የሲዳማ ክልል በዋናነት በአራት ዞኖች ይደራጃል ብለዋል።
የሚደራጁት ዞኖች ባህሪ ምክር ቤትና ብዛት ያላቸው መስሪያ ቤቶች የሚኖራቸው ሳይሆን 30 ወረዳዎችን በመፍጠርና የመረጃ ፍሰቱን በማቀላጠፍ በቅርበት ድጋፍ እንዲሰጡ የሚደረግ መሆኑን አመልክተዋል።
በስድስት ካቢኔ ደረጃ የሚዋቀር እና አስተባባሪ ያለው አንድ ዞን ከ50 የማይበልጥ የሰው ኃይል ያለው ሆኖ ዋና ተልእኮው ክልል እና ወረዳን ድልድይ ሆኖ ማገናኘት እንደሚሆን አስታውቀዋል።
ለጊዜው ተጨማሪ ወረዳን ለመክፈት ጥናቱ እንደማያሳይ ጠቁመው፣ ወረዳን እያሰፉ መሄድ ወጪን ማብዛት እንጂ ሕዝቡ የሚፈልጋቸውን መሠረታዊ የሆኑ የመንገድ፣ ውኃ፣ ጤና፣ ትምህርት እና ሌሎችንም አቅርቦት ለሟሟላት አያስችልም ብለዋል።
ርእሰ መስተዳድሩ "ክልል መሆን በራሱ ትልቅ ሀብት የሚያስገኝና የፈለጉትን ማድረግ የሚያስችል አድርጎ የሚያዩ ወገኖች አሉ፤ እኛ ግን ይህ እንዳልሆነ በፊትም እናውቃለን፣ አሁንም በተጨባጭ እያየን ያለነው ይሄንኑ ነው" ብለዋል።
ባለው ውስን ሀብት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ድህነትን መዋጋት፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈንና የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ቅድሚያ በመስጠት ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ደስታ ገለፃ በሚቀጥሉት ዓመታት የትኩረት ማእከል ሆኖ የሚቀጥለው ወጣቶችን የልማት ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ማድረግ ነው።
በተመረጡ ዘርፎች ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማደራጀት በልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እና በሌሎችም ገበያ ተኮር በሆኑ የሥራ መስኮች ለማሰማራት ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
©Ebc
Comments
Post a Comment