በአሜሪካው አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ድርጅት አዘጋጅነት ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ተወስኖ ዝግጅት ሲደረግበት የከረመው የቡና ጥራት ውድድር ወይም ‹‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ›› ውድድር በኮሮና ምክንያት በተፈጠረ የበረራ ክልከላና በሎጂስቲክስ ችግሮች ምክንያት ተሰርዞ በአሜሪካ እንዲካሄድ መወሰኑ ታወቀ፡፡
አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታቀደው የቡና ጥራት ቅምሻ ውድድር በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ ዳኞች አወዳዳሪነት እንዲካሄድ ሰፊ ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ የቡና ናሙና በማቅረብ የኢትዮጵያ ቡና አምራቾች ሪከርድ የሰበሩበትን ተሳትፎም አስተናግዶ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተጎጂዎችን ያጠቃውና ከ60 ሺሕ በላይ ለሞት የዳረገው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የዓለም ኢኮኖሚ በማሽመድመድ ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ዝግጅት ሲደረግበት የሰነበተውና ዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጠው የቡና ጥራት ውድድርም የኮሮና ሰለባ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣንና በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) ሥር ፊድ ዘ ፊውቸር የተሰኘው ተቋም ሲያስተባብሩት የቆየው ዝግጅት ወደ አሜሪካ እንዲዘወር መደረጉን አዘጋጁ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም የቡና ጥራት የቅምሻ ውድድሩ በፖርትላንድ፣ ኦሪገን እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡
ምንም እንኳ የመጨረሻው የጥራት ውድድር በበረራ ክለከላና በሎጂስቲክስ ችግሮች ምክንያት በኢትዮጵያ ባይካሄድም፣ ለውድድሩ የቀረቡ ናሙናዎች ወደ አሜሪካ ተልከውና በላቦራቶሪ ተፈትሸው አሸናፊዎቹ ናሙናዎች ለባለቡናዎቹ እንዲገለጹ የሚደረግበት ተለዋጭ ዕቅድ መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡
ለዚህ ተግባር የሚጠበቁ ዳኞችን በሙሉ ማሳተፍ ባይቻልም፣ የተመረጡና ልምድ ያላቸው የዳኞች ስብስብ ከኢትዮጵያ የተላኩትን የቡና ናሙናዎች እንደሚመዝኑም ተገልጿል፡፡
ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በጥራት ቅምሻው ውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከጥር 25 ቀን እስከ ጥር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በጅማ፣ በሐዋሳ፣ በድሬዳዋና በአዲስ አበባ ለውድድር የሚቀርቡ ቡናዎችን ለመሰብሰብ ወደተዘጋጁ ማዕከላት ከ1,450 በላይ የቡና ናሙናዎች ገቢ ተደርገው ነበር፡፡
የኮሮና ቫይረስ ያጠላበት ይህ ውድድር ከፍተኛ የቡና ናሙና ለውድድር የቀረበበትና ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የቀረበ ከፍተኛው አኃዝ ቢሆንም፣ በወረርሽኙ ሥጋት ምክንያት በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን፣ በሌሎች ከአሥር ያላነሱ አገሮች ሊካሄድ የታቀደው የቡና ቅምሻ ውድድር ሊሰረዝ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ የጥራት ቅምሻ ውድድሩ በ11 ቡና አምራች አገሮች ውስጥ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡
የባለልዩ ጣዕም ቡናዎች የጥራት ውድድር ላይ እስካሁን ከተመዘገበው ይልቅ ለመጀመርያ ጊዜ የታየና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቡና ናሙና ቀርቧል፡፡
ውድድሩ እ.ኤ.አ. በ1999 በብራዚል ተጀምሮ፣ በኮሎምቢያ፣ በፔሩ፣ በኤልሳልቫዶር፣ በኮስታሪካ፣ በኒካራጓ፣ በጓትማላ፣ በሆንዱራስ፣ በሜክሲኮ፣ በብሩንዲና በሩዋንዳ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ የቡና ጥራት በዓለም አቀፍ ዳኞችና በኢትዮጵያውያን ተሳትፎ የሚካሄድ የልዩ ጣዕም ቡናዎች የቅምሻ ውድድር ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶ ነበር፡፡ ተወዳዳሪዎች በተለይም ቡና አምራች ገበሬዎች በጥንቃቄ ጥራት ያለው ቡና እስካቀረቡ ድረስ የተሻለ ዋጋ እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡ አቀናባሪዎችና ሌሎችም የቡና ኢንዱስትሪ ተሳታፊዎች የተሻለ ገበያና ዋጋ እንደሚያገኙ ስለሚታመን በውድድሩ ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ ከሚጠበቁት መካከል ናቸው፡፡ ውድድሩ የዓለም የቡና ኢንዱስትሪ ተዋንያንና ሚዲያዎችን ትኩረት ስለሚስብ ዕውቅ የኢትዮጵያ ቡናዎች የበለጠ ዕውቅና ማግኘት የሚችሉበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም እንዳስታወቀው፣ የውድድሩን የመጀመርያ ዙር የሚያልፉ ናሙናዎች ወደ አዲስ አበባ ተልከው በአገር ውስጥ ቀማሾች የጥራት ደረጃቸው ይለካል፡፡ ከእነዚህ ቡናዎች ውስጥ 150 አሸናፊዎች ተመርጠው በአገር ውስጥ ቀማሾች በድጋሚ ተቀምሰው፣ 40 የላቁ ቡናዎች ለመጨረሻ ዙር ውድድር ያልፋሉ፡፡ ውድድሩን የሚዳኙት ከመላው ኢትዮጵያ ተውጣጥተውና ተገቢውን ሥልጠና ወስደው ብቃታቸው የተረጋገጠላቸው ዳኞች ሲሆኑ፣ ከተለያዩ አገሮች የሚሳተፉት ዳኞችም በሌሎች አገሮች የተካሄዱ ውድድሮች ላይ የተሳተፉና የዳኙ፣ ልምዱና ዕውቀቱ ያላቸውን ቡና ገዥዎችና ዳኞችን ያካተተ ስብስብ ስለመሆኑ የባለሥልጣኑ መረጃ ይጠቅሳል፡፡
በጥራታቸው አሸናፊ የሚሆኑ ቡናዎች፣ ውድድሩ በተካሄደ በስድስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ድረ ገጽ አማካይነት በሚከናወን ዓለም አቀፍ ጨረታ አማካይነት ለገዥዎች እንደሚሸጡ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ውድድሮች በጥራት አሸንፈው የተሸጡ ቡናዎች በተደጋጋሚ የዓለም የቡና ዋጋ ሪከርድ መስበራቸው ይጠቀሳል፡፡ ከየካቲት 16 ቀን እስከ የካቲት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለውድድር በገቡት ቡናዎች ላይ የቅድመ መረጣ ሥራ እንደሚከናወን፣ ቡናዎችን ወደ መጋዘን የማስገባት ሥራውም ከየካቲት 23 ቀን ጀምሮ እስከ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚከናወን፣ አገር አቀፍ ውድድሩም ከመጋቢት 21 ቀን እስከ መጋቢት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ብሎም ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኩ ከመጋቢት 29 ቀን እስከ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚከናወን ይጠበቅ ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ የሽያጭ ጨረታው በግንቦት እንደሚካሄድ ባለሥልጣኑ ይፋ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን የዚህ ውድድርና የሽያጭ መርሐ ግብር ብቻም ሳይሆን፣ ከአገሪቱ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የቡና ምርትም ከፍተኛ የገበያ ችግር ተጋርጦበታል፡፡ ሥጋታቸውን ከወዲሁ ለሪፖርተር የገለጹ ላኪዎች በበሽታው ወረርሽኝ ሳቢያ በርካታ አገሮች የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ እየጣሉና ዕገዳ እያወጡ በመሆናቸው ሳቢያ፣ የዘንድሮው የቡና የወጪ ንግድ ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ሥጋት አድሮባቸዋል፡፡ በዚህ ዓመት ከ300 ሺሕ ቶን ያላነሰ የቡና ምርት ለውጭ ገበያ ቀርቦ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ሊገኝ መታቀዱ ይታወቃል፡፡
በቅርቡ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ይፋ ባደረገው መረጃ፣ በስምንት ወራት ውስጥ ለውጭ ከቀረበ ከ167 ሺሕ ቶን በላይ የቡና ወጪ ንግድ ከ465 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘቱ ታውቋል፡፡ ከታቀደው የገቢ መጠን ከ100 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ቅናሽ አስተናግዷል፡፡
ባለሥልጣኑ ለሪፖርተር ልኮ በነበረው መግለጫ መሠረት፣ ለውጭ ገበያ የቀረቡት ቡናን ጨምሮ የሻይና የቅመማ ቅመም ምርቶች ሲሆኑ፣ በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ውስጥ 176,249.80 ቶን የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ውጤቶችን በመላክ 577.70 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የዕቅዱን 100 በመቶ ያሳካበትን የ176,360.82 ቶን ምርት አፈጻጸም በማስመዝገብ የምርት አቅርቦቱን ቢያሳካም፣ በገቢ ረገድ ግን የሁሉም ምርቶች ውጤት ከ478 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 81 በመቶ ያህል ገቢ አስገኝቷል፡፡
ከዚህ አፈጻጸም ውስጥ የቡና ድርሻ በምርት ብዛት መጠን 167,132 ቶን ነበር፡፡ ከዕቅድና ከአፈጻጸም አኳያ ሲዘመን፣ ከ2011 ዓ.ም. ስምንት ወራት አኳያ፣ በመጠን ረገድ የ37,893.22 ቶን ወይም የ27.37 በመቶ፣ በገቢ በኩልም የ28.2 ሚሊዮን ዶላር ወይም 6.3 በመቶ ጭማሪ ማስመዝገቡ ተጠቅሷል፡፡
በስምንት ወራት ከተላከው የቡና ምርት ውስጥ 138 ቶን ቡና እሴት ተጨምሮበት ለውጭ ገበያ ሲቀርብ፣ ከገቢ አኳያም ከ900 ሺሕ ዶላር ገደማ አስገኝቷል፡፡
Comments
Post a Comment