የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጪው ነሐሴ ወር ሊካሄድ ታስቦ የነበረውን አጠቃላይ ምርጫ በተመለከተ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ መክሮ ውሳኔ ለማሳለፍ፣ ሐሙስ ሚያዚያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ይሰበሰባል። ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አንድ የሪፖርተር ምንጭ እንደገለጹት፣ የፓርላማው ስብሰባ የሚያተኩረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮ አጠቃላይ ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በመጪው ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ለማካሄድ እንደማይችል በመግለጽ፣ ፓርላማው ውሳኔ እንዲሰጥበት ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ ለመወሰን ነው። በዚሁ መሠረት ምርጫ ቦርድ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫውን ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ማካሄድ እንደማይችል ያቀረባቸውን ዝርዝር ምክንያቶች፣ እንዲሁም ቦርዱ ለፓርላማው የመፍትሔ ውሳኔ መነሻ ከሆነ ብሎ ያሰናዳውን በዳሰሳ ጥናት ላይ የተመሠረተ የቢሆን መፍትሔ አማራጭ በምክር ቤቱ በአካል ተገኝቶ እንደሚያቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን በሌላ ጊዜ ለማካሄድ በመፍትሔ አማራጭነት የሚያቀርባቸውን ሐሳቦች ምክር ቤቱ ካዳመጣ በኋላ፣ በሕገ መንግሥቱ ዓውድ ውስጥ ተገቢ የሚሆነው ሕጋዊ ውሳኔ ሊወሰን እንደሚችል ይጠበቃል። የፓርላማው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት በመጪው ሐሙስ መደበኛ ስብሰባ እንደሚካሄድ ለሪፖርተር የገለጸ ቢሆንም፣ ውይይት ስለሚደረግበት አጀንዳ ግን መረጃ እንደሌለው አስታውቋል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መግለጫ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት በፈጠራቸው ተግዳሮቶች፣ እንዲሁም በዚህ ምክንያት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ባወጧቸው ክልከላዎች ምክንያት ምርጫውን በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ማከናወን እንደማይችል ማስታወቁ ይታወሳል። በዚህ የተነሳም ለም
It's about Sidaama!