ዛሬ የሲዳማን ህዝብ ድምጽ ያፈነው የፌዴራል መንግስት፤ ነገ የአንተን የምርጫ ድምጽ ላለማፈኑ ምንም ማረጋገጫ የለም


ለሲዳማ እና ለሲዳማውያን የወቅቱ አንገብጋብ አጄንዳ የስልጣን ርክብክብ ነው። እንደሚታወቀው የስልጣን ርክብክቡ ከሲዳማ አመራሮች እና የደቡብ ክልል ባለስልጣናት አቅም በላይ ሆኗል። ሰሞኑን እንደሰማነው ከሆነው፤ ደቡብ ተብዬውን ክልል ለአራት ለመክፈል ህዝቡን ለማሳመን የቀድሞ የደኢህዴን ካድሬዎች፤ ብሎም ያሁኑ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ቀን ከሌሊት በመስራት ላይ ናቸው።

በዚሁ ፕሮግራም ውስጥ ሲዳማም እንደ አዲስ ክልል ሳይሆን በቀድሞ ደረጃው ከጌዴኦ ዞን ጋር አንድ በሚሆንበት ሁኔታ ላይ ህዝብን ለማወያየት እቅድ ተይዞአል። እቅዱ ተግባራዊ መሆን አለመሆኑ በሲዳማ ህዝብ ምላሽ እና አሁን በስልጠና ላይ ባሉት የሲዳማ ተወካዮች ይሁንታ ይወሰናል የሚል እምነት አለኝ።

የአገሪቱ መንግስት ለህገ መንግስቱ ያለው ንቀት፤ እንደህዝብ የሲዳማን ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመመለስ የወጣውን ከፍተኛ የአገር ሀብት ማለትም፤ ከፍተኛ ገንዘብ እና ጊዜ የፈሰሰባቸውን ዴሞክራሲያዊ ተግባራትን በምሳሌነት መውሰድ እና በተቀሩት ዴሞክራሲያዊ እርከኖች ተግባራዊ ማድረግ ሲገባ፤ በተቃራኒው በመስራት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በሚቀጥለው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ ምንም አይነት ዴሞክራሲያዊ መንገድ ተከትሎ መብቱን በድምጹ ብያረጋግጥ እንኳን መብቱ ልከበርለት እንደማይችል የሲዳማ ክልል ህዝበ ወሳኔ አንድ ማሳያ እየሆነ ነው።

የሲዳማን ህዝብ የክልል አስተዳደር ምስረታን ለማኮላሽት ማእከላዊ መንግስት ያልፈነቀለው ድንጓይ የለም። አሁን አሁንማ በሃይማኖት አማካኝነት ለሲዳማ ህዝብ መብት እና አርነት የሚታገሉትን ታጋዮች፤ በሀይማኖት ሰበብ መንቀሳቀሻ በማሳጣት እና በሚቆጣጠራቸው እና በሚታዘዙት ፌክ ፓስተሮች አማካይነት ከፍተኛ ክትትል እንዲደረግባቸው በማድረግ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንድቀንሱና የሚከተሏቸው ደጋፊዎቻቸው በእነርሱ ተስፋ እንዲቆርጡ በመስራት ላይ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለሲዳማ ህዝብ ተቆርቃሪ የሆኑ የሲዳማ ተወላጅ የፌደራል መንግስት የህዝብ አገልጋዮችን በሰበብ አስባቡ ከስራ ገበታቸው ከማንሳት አልፎ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከሲዳማ ህዝብ የማራቅ ተግባራትን ተያይዟል።

የሲዳማ ህዝብ በርግጥ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉት። ከዚህም ባሻገር በሲዳማ የልማት ስራዎችን ማየት ታሪክ ሆኗል። በሌሎች ክልሎች በየአጋጣሚዎ ሜጋ ፕሮጄክቶች ስመረቁና ለግንባታ የመሰረት ድንጓዮች ስጣሉባቸው በሲዳማ የዛሬ አስራ አመታት የተሰሩ የመንገድ ስራዎች ካልሆኑ በስተቀር ምንም አዲስ ልማት አይታዩም። የሲዳማ ህዝብ ከዛሬ 15 አመታት ከነበረበት አኳያ እንኳን ብታይ የድህነት መጠኑ ጨምሯል። ከዛሬ 15 አመታት በፊት ከነበረው በላይ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በከፍተኛ ድህነት ይኖራል።

በሀዋሳ ከተማ በጎዳና ተዳዳሪ የሲዳማ ልጆችን ቁጥር ከዛሬ አስር አመት በፊት ከነበረው ጋር ማነጻጸር፤ የሲዳማ ህዝብ ምን ያህል በኢኮኖሚያዊ ልማት አንጻር በአገሪቱ መንግስት ችላ እንደተባለ ማሳያ ነው። የሲዳማ ህዝብ ላለፉት በርካታ አመታት ግንባር ቀደም የትግል ጥያቄው ነጻ መውጣት እና የራሱን ክልል መመስራት በመሆኑ ትኩረት ባለመስጠቱን እንጂ፤ ከልማት አንጻር በምእተ አመታት ከተቀረው የአገሪቱ ህዝብ ወደ ሓላ ቀርቷል።

የሲዳማ ህዝብ ያሉበትን የመልካም አስተዳደር እና የልማት እጦት ችግሮቹን ዋጥ አድርጎ፤ ለዘመናት ያደረገውን የክልል ጥያቄ ወደ ሓላ ለመቀልበስ የሚደረገውን ማንኛውንም አይነት የፌደራል መንግስት ጠልቃ ገብነት፤ ማንም ህልና ያለው ሁሉ ልቃወም ይገባል። ዛሬ የሲዳማ ህዝብ ድምጹን በፌዴራል መንግስት ሲቀማ እያየ እንዳላየ ዝምታን የመረጠው ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ነገ በራሱ መሰል ተግባር ላለመደገሙ ዋስትና ስለሌው ከሲዳማ ህዝብ ጎን ቆሞ ለህዝቦች ድምጽ መከበር ድምጹን ልያሰማ ይገባል እላለው።


No comments