29 ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ የጫነ አንድ ተሸከርካሪ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ገልፀ፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ ኮለኔል ሮዳሞ ኪአ እንዲሁም ኮማንደር ኢዮብ አቤቶ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም መሰረት ትላንት ምሽት 5፡00 አካባቢ ኮድ 3/ 34480 አ.አ ታርጋ ቁጥር በለጠፈ አይሱዙ ኤፍ.ኤስ.አር ተሸከርካሪ 29 ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በመኪናው ከፋብሪካ ውጭ በተሰራ በቀላሉ የማይገኝ ሚስጥራዊ ቦታ ተደብቆ ሲጓዝ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፀዋል፡፡
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያውን ሲያጓጉዙ የነበሩት የመኪናው አሽከርካሪ፣ የህገ-ወጥ ጦር መሳሪያው ባለቤት እና የመኪናው እረዳት በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተገልጿል፡፡
ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መረጃው ከሳምንት በፊት አስቀድሞ በደረሰ ጥቆማ የታወቀ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ብቃት ያለቸውን የፖሊስ አመራሮች በመመደብ ጉዳዩ በሚስጥር ሲጣራ ቆይቶ ትላንት ምሽት በቁጥጥር ስር መዋሉ ነው የተገለፀው፡፡
የጦር መሳሪያው ከየት ተነስቶ ወደየት እንደሚሄድ ለምን ዓላማ ሊውል እንደተፈለገ ጭምር መረጃዎች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን ጉዳዩ በምርመራ ሂደት ላይ በመሆኑ ሳይገለፅ ቀርቷል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ የፀጥታ ሀይሉን አቅም በማጠናከር እና ከህዝብ ጋር በመቀናጀት ማንኛውንም አይነት ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ሮዳሞ ኪአ ገልፀዋል፡፡
በዚህም የከተማዋ ሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እና እየተጠናከረ መምጣቱን ኮለኔል ሮዳሞ ገልፀው ሀዋሳ ከተማ ከቀድሞ በተሻለ የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ ውስጥ መሆኗን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በፖሊስ መዋቅሩ ይታዩ የነበሩ ጉድለቶችን በመለየት፣ በማጠናከር እና ለውጥ በማድረግ የነበሩ ጥንካሬዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሲሰራ መቆየቱን ኮማደር ኢዮብ አቤቶ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ገልፀዋል፡፡
የወንጀል መከላከል እና የፀጥታ ስራውን ህዝባዊ ማድረግ በመቻሉ በከተማዋ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን ከማስቆም ረገድ ውጤታማ ስራ መስራት ተችሏል ያሉት ኮማንደር ኢዮብ በዚህም ኮንተሮባንድን ከመቆጣጠር ረገድ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች እየተቀረፉ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በዚህም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተሰጠው ትኩረት መሰረት በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ በርካታ የምግብ ዘይት፣ ከ13 ቦንዳ በላይ ልባሽ ጨርቅ፣ ህገ-ወጥ መድሀኒት፣ በርካታ ኩንታል ቦለቄ የመሳሰሉ በሀገር እና በከተማ ማህበረዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፉ የሚችሉ የኮንትሮባንድ እና ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮማደር ኢዮብ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
Comments
Post a Comment