ለደቡብ ክልል አፈ-ጉባዔ ጽ/ቤት
ሀዋሳ፤
ጉዳዩ፡- በህገ-መንግስቱ መሠረት የሥልጣን ርክክብ እንዲደረግ ስለማሳሰብ፤
=========
አንደሚታወቀው ሁሉ የሲዳማ ህዝብ ለዚህች አገር ሰላም፣መረጋጋትና አንድነት የራሱን የታሪክ አሻራ ያኖረና በአንፃሩም ደግሞ በየዘመኑ የሚፈራረቁ አምባገነን የኢትየጵያ ገዢዎች የሚያደርሱበትን በደልና አፈና በጽናት ስታገል የቆየ ህዝብ እንደሆነ ታሪካዊ ሀቅ ነው፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የሀገሪቷን ሥልጣን ኮርቻ የሚቆናጠጡ ገዢዎች ሲዳማን ሳይሆን የሲዳማን ሀብት ለመቀራመት ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የህዝቡን ቋንቋ፣ታሪክ፣ ባህልና ማኅበራዊ አሻራና ማንነት ለመናድ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡የሀገር ግንባታ ሂደት የማንነት ፈተና በማይሆንበት መልኩ መስራት ይቻላል የሚል ጠንካራ አቋም ማራመድ የጀመሩት የሲዳማ ቀደምት ታጋዮችና ሌሎች የትግል አርበኞች በከፈሉት የህይወት ዋጋ ላለፉት 28 አመታት ስራ ላይ የዋለው ህገ-መንግስታዊ ሥርዓት እውን ሆኗል፡፡


ምንም እንኳን የሲዳማ ህዝብ የጭቁን ብሔሮችን ድምጽ አስተጋብቶና ታግሎ ለ1987 ዓ.ም ህገ-መንግስት ታሪክ የማይረሳ አሻራውን ለማሳረፍ ቢበቃም የሲዳማ ምድር እንጅ የሲዳማ ህዝብን አምርረው በሚጠሉ ገዢ መደቦች በተጠነሰሰ ሴራዎች ህዝባችን የህገ-መንግስቱ ትሩፋት ተቋዳሽ እንዳይሆን በመታገዱ ምክንያት ለቀጣይ ሰላማዊ የትግል ምዕራፍ ለመቀጠል ተገዶአል፡፡


በገዛ ሀገሩ ወደ ዳር የተገፋና በይ ተመልካች ሆኖ ለዘመናት የቆየው ሰፊው የሲዳማ ህዝብ በደሙና ባጥንቱ የተጻፈው ህገ-መንግስት ሊታደገው ባለመቻሉ ለሞት፣ ለስደትና ለእስራት ቢዳረግም ቅሉ ህዝብን ግን ከትግል ወደ ኋላ ሊያስቀረው አልቻለም ፡፡


በመሆኑም ከአባቶች የተወረሰ መብትን የማስከበር የትግል ወኔ ለዚህ ዘመን ትውልድ በመድረሱ አዲሱ ትውልድም የትግል ችቦውን በማቀጣጠል ላለፉት ሁለት ዓመታት ታዓምራዊ ክስተት በሲዳማ ምድር አሳይቷል፤ የዓለምን ማኅበረሰብ የሚያስደምም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ተካሂዷል፤ በውጤቱም ህዝባችን በፖለትከኞች ሴራ ቅርቃሪ ሲበጅለት የነበረውን እራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግስታዊ በክልል የመደራጀት ጥያቄን በህዝብ ይሁንታ እንዲረጋገጥ ማድረጉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡


በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 47 ላይ በዝርዝር የተቀመጡ ተግባራት ከብዙ ፈተናዎች ሲጠላለፍ ቆይቶ በህዝባችን ብርቱ ትግልና በለውጡ ኃይል አጋሪነት ተፈጻሚ ሲሆን አሁን የቀረው ከነባሩ ክልል ም/ቤት ስልጣን ለጠየቀው ህዝብ ም/ቤት የማስረከብ ተግባር ብቻ ነው፡፡


ሉዓላዊ የሆነው ህዝብ ድምጹን ሰጥቶ የሚጠበቅበትን አከናውኖ ሲያበቃ ቀሪው ህገ-መንግስታዊ ጉዳይ ገቢራዊ በማድረግ ረገድ ከደቡብ ክልል ም/ቤት በኩል ማድረግ ያለበትን ርክክብ እስከ ዛሬ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ዝም መባሉ ተቀባይነትና አግባብነት እንደሆነ ሲአን ያምናል፡፡


ህገ-መንግታዊ ስርዓትን ተከትሎ በህዝባችን ተሳትፎና ዉሳኔ ይሁንታ ያገኘዉን የሲዳማ ብሔር በክልል የመደራጀት ጉዳይ በፖለቲካዊ እና በጎንዮሽ ድርድር ለመተካት የሚደረገው ሙከራ የሰፊውን የሲዳማን ህዝብ አሳንሶ የማየት አባዘ መሆኑን ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡


ስለሆነም በህገ-መንግስቱ በግልጽ በተቀመጠው ሥነ-ስርዓት መሠረት ከህዝበ-ውሳኔ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ፖለቲካዊና የጎንዮሽ ድርድር ድርጅታችንና ህዝባችን አጥብቆ የሚያወግዘው፤ የሚቃወመውና በሰላማዊ መንገድ የሚታገለውም እንደሆነ ከወዲሁ እየገለፅን በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ሥልጣን የማስረከብ ኃላፊነት የተጣለበት የደቡብ ክልል ምክር ቤት ከዚህ በፊት ህዝብን ወክሎ በህገ-መንግስቱ የተጣለበትን ህዝባዊ አደራ በጊዜ ገደብ ባለመፈጸሙ ምክንያት በአካባቢያችን ተፈጥሮ ከነበረው ችግር ትምህርት በመዉስድ ዳግም ለታሪካዊ ስህተት በማይዳርገው መልኩ ሥልጣንን ለብሔሩ ም/ቤት እንዲያስረክብ አበክረን እያሳሰብን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለሚፈጠሩ ህዝባዊ ቁጣዎችና ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት የክልሉ ም/ቤት መሆኑን ከወዲሁ ለማስገንዘብ እንፈልጋለን፡፡


ከሠላምታ ጋር!ግልባጭ
ለደቡብ ክልል መስተዳደር ጽ/ቤት
ለሲዳማ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት
ለሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት
ሀዋሳ

No comments