የሲዳማ ህዝብ ላለፉት 130 ዓመታት ለብሄር ብሄረሰቦች እራስን በራስ የማስተዳደር መብትና ለሉኣላዊ የስልጣን ባለቤትነት እውን መሆን መራራ ትግል ሲያደርግ እንደቆየ ይታወቃል።
አሁን ላይ ለረጅም ግዜ ሲደረግ የነበረው ትግል ወደ ወሳኝ የድል ምዕራፍ ተሸጋግሯል። የተገኘውን ድል ጠብቆና አድምቆ ለመሄድ የተደራጀና ህዝባዊ መሰረት ያለው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። ሆኖም አሁን ያለው አከባቢያዊና ሀገራዊ የፖለቲካ እውነታ ህዝባችን እና ያገኘውን ድል የሚመጥን ከመሆን በተቃራኒ ህዝባችን በጠየቀው ጥያቄ እንዲሸማቀቅና ጥፋተኝነት እንዲሰማው በማድረግ ከፍተኛ የሆነ የብቀላ ወጥመድ እየተዘረጋ ያለበትን ሁኔታ አስተውለናል። ህዝባችንን ዳግም በጨለማ ለመወርወር እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ከግዜ ወደ ግዜ መልካቸውንና መጠናቸውን እየቀየሩ በህዝባችን ላይ ከፍተኛ የሆነ የሞራል እና የስነ ልቦና ጫናዎችን እየፈጠሩ ቆይተዋል። ለአብነትም የሲዳማ ህዝብ ብዙ ዋጋ ከፍሎ ያገኘው በክልል የመደራጀት መብት የስልጣን ርክክብ እንዳይደረግና እንዲዘገይ ከዛም ባሻገር ከህዝባችን ፍላጎትና ውሳኔ ውጪ የሆነ ፖለቲካዊ መዋቅር ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ሙከራ የዚህ ሴራ ማሳያ ነው። ከዚህም ባለፈ ህዝባችን ድል ሊያስጠብቅ የሚችለውን ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊና ህገ መንግስታዊ ስርዓትን አጠልሽቶ ለማሰናከል እየተደረገ ያለው ጥረት ይህ ነው የሚባል አይደለም።
ለዚህ ሴራ ትግበራ ይሆን ዘንድ የሲዳማ ፖለቲካ ሊህቃኖችን፥አክቲቪስቶችን እና ጋዜጠኞች ላለፉት 7 ወራት ያለ ፍርድ በእስር እንዲሰቃዩ ተደርጎ የሚመሰረተውን የሲዳማ ክልል አቅም አልባና ደካማ አድርጎ ለማቅረብ የተኬደው ርቀት ከፍተኛ ነው። በህዝባችን ላይ እየተካሄደ ያለው ይህ ሁሉ የብቀላ ዘመቻ "ምን ያመጣሉ" ከሚል ስሜት የመነጨ የንቀት ዱላ መሆኑን ተገንዝበናል።
ይህ በመሬት ላይ ያለው እውነታና በቀጣይነት የሚኖረው የህዝባችን እጣ ፈንታ ባሳሰባቸው የሲዳማ ምሁራን አነሳሽነት(አስተባባሪነት) የተጠነሰሰው ኤጄቲማ ፌደራሊስት ፓርቲ በርካታ ስራዎችን በውስጥ ሲሰራ ቆይቶ ከብዙ አይነት ዛቻዎችና የማጥቆር ፕሮፓጋንዳዎች አልፎ ዛሬ ወደ ወሳኝ ተቋማዊ ደረጃ ተሸጋግሯል። ፓርቲው በአስር አስተባባሪ( አነሳሽ ) ወገኖች የተጀመረ ሲሆን በቅርቡ የአባላት ምዝገባውን አጠናቆ መስራች ጉባኤ በመጥራት በይፋ ይመሰረታል። በዚህም ጉባኤ ከፓርቲ ስያሜ፣ ከፖለቲካ ርዕዮት፣ ከፓርቲ አመራሮችና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እልባት ያገኛሉ። ፓርቲው እንደ አስፈላጊነቱ ከተለያዩ አካላት ( ፓሪቲዎች ) ጋር በፎረም፣ በቅንጅት አልያም በግንባር ሊሰራ የሚችልባቸው ሁኔታዎች የተጠበቁ ሲሆን ተራማጅ ፌደራሊስታዊ አቅጣጫን የሚከተል መሆኑን ሁሉም ሊያወቀው ይገባል እንላለን።
ከጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ
ጥር 21/2012 ሲዳማ፣ ሀዋሳ፣ ኢትዮጵያ
Comments
Post a Comment