በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በአካባቢ የልማት ጥናት መሰረት በዩኤልዲፒ የልማት ስራ ለሁለት ዙር ተነሺዎች ምትክ ቦታ በእጣ የማስተላለፍ ስራ እንደተሰራ ይታወቃል፡፡
በዛሬው እለትም ለሶስተኛ ዙር በታቦር ክ/ከተማ ፋራ ቀበሌ በመንገድ ልማት ተነሺ ለሆኑ 122 ነባር ባለይዞታዎች በዶሮ እርባታ አካባቢ በተዘጋጀ መሬት እንደየ መሬት ይዞታቸው በዕጣ በመለየት ምትክ ቦታ የማስተላፉ ስራ ተከናወኗል፡፡
እስከ አሁን ለ240 ነባር ባለይዞታ አርሶ አደሮች ምትክ ቦታ የተሰጣቸው ሲሆን በአጠቃላይ 1136 ተነሺዎችን ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በተዘጋጀላቸው ቦታ በማሳረፍ ሙሉ በሙሉ የመንገድ ከፈታ ስራዎችን በመስራት የህብረተቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ከተማ አስተዳደሩ እየሰራ መሆኑን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ተናግረዋል፡፡
አቶ ጥራቱ ከዚህ ቀደም በተላለፉ ቦታዎች አካባቢ የተከናወኑ ተግባራትን በስፍራው ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን ልማቱን ሊያፋጥኑ የሚችሉ አሰራሮች እንደሚተገበሩም ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ በጎርፍ ምክንያት የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ በዋርካ ሆቴል እና በሳውዝ ስታር አካባቢ የተጀመሩ የጎርፍ ውሃ መውረጃ ቦዮች በተፈለገው ፍጥነት ያልተጓዘ መሆኑን የተናገሩት ከንቲባ አቶ ጥራቱ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ህብረተሰቡ መታገስ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ የሀዌላ ቱላ ክ/ከተማን ጨምሮ የመንገድ፣ የመብራት፣የውሃ፣ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም፣ የጎዳና ልጆችን በማሰልጠን እና ሌሎች መልካም አስተዳደር እና የልማት ስራዎች ላይ ከተማ አስተዳደሩ በየደረጃው ለማከናወን በበጀት ተደግፎ ተግባራት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በመንግስት ተቋማት ውስጥ ያሉ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድም የተለያዩ ማስተካከያዎች መደረጉን የተናገሩት አቶ ጥራቱ ከዚህ ባለፈም ችግር ያለባቸው አካላትን በህግ የማስጠየቅ ስራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡
በእጣ የማውጣት ስፍራ ከተገኙ የልማት ተነሺዎች መካከል አንዳንዶቹ እንደተናገሩት አሁን እየተከናወነ ያለው ተግባር የረጅም ዓመታት ጥያቄ ከመሆኑም በላይ በመንገድ፣በውሃ እና ለእለት ተእለት ማህበራዊ ግንኙነት ጭምር ትልቅ ተግዳሮት እንደነበረ አስታውሰው ከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ሲጠይቁ ለተጀመረው የልማት ስራ አጋዥ እንደሚሆኑ በመግለጽ ነው፡፡
Comments
Post a Comment