የአንበጣ መንጋ ክስተት ከተስተዋለ ብኋላ ህብረተሰቡ እየወሰደ ያለው የጥንቃቄ እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገለፀ፡፡
እንደከተማ የአንበጣ መንጋው ተበታትኖ በሶስት አቅጣጫ የታየ መሆኑ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ያግዛል ያሉት አቶ ፍቅረየሱስ አሸናፊ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ ናቸው፡፡
ይሁንና መንጋውን ለማባረር ነዋሪው በሚያደርገው ያላሰለሰ እንቅስቃሴ ከከተማ እንዲወጣ ካልተደረገ የከፋ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን አቶ ፍቅረየሱስ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ንፋስ የሌለ መሆኑ መንጋው የንፋሱን አቅጣጫ ተከትሎ እንዲወጣ ንፋሱን ተከትሎ ጭስ ማጨስ እና ድምፅ ማሰማት አለመቻሉ በዚህም በዚያም ጭስ ማጨሱ እና ድምፅ የማውጣት ስራ መሰራቱ አስቸጋሪ ያደረገው መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ለሰው እና ለእንስሳት እንዲሁም ለከተማ ግብርና ስራ የሚመከር ባለመሆኑ የኬሚካል ርጭት ማድረግ ቀላል አለመሆኑን የገለፁት አቶ ፍቅረየሱስ ህብረተሰቡ በሚያደርገው ጥረት መንጋውን ማባረር ካልተቻለ በተኩስ የሚሞከር መሆኑን ነው አቶ ፍቅረየሱስ ጨምረው የገልፁት፡፡
በተለይ በከተማ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የሰው እንቅስቃሴ ያለ በመሆኑ የአንበጣ መንጋውን በጪስ እና በተለያየ መንገድ ለማባራር ሙከራ እየተደረገ መሆኑ የሚበረታታ መሆኑን አቶ መልካሙ ተፈራ የከተማ አስተዳደሩ ህዝብ ግንኙነት ጽ/ቤት ኃላፊ ገልፀዋል፡፡
የሰዎች እንቅስቃሴ የሌለባቸው አካባቢዎች በተለይ እንደ ጉዱማሌ ፓርክ፣ ሚሊኒየም ፓርክ እና ሌሎች ስፋት ያላቸው እና የሰዎች እንቅስቃሴ የማይታይባቸው አካባቢዎች ላይም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ነው አቶ መልካሙ ጨምረው የገለፁት፡፡
በሌላ በኩል አንበጣውን ለማባረር በሚደረገው ጥረት ጭስ ለማጨስ የሚለኮስ እሳት ሌላ አደጋ እንዳያስከትል ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል ያሉት አቶ መልካሙ ተፈራ ከሀዋሳ የሚባረረው የአንበጣ መንጋ አልፎ የሚሄደው ወደአጎራባች ከተሞች በመሆኑ አጎራባች ከተሞች ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
Comments
Post a Comment