የሲዳማ ህዝብ ለዘመናት ባደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል እና በከፈለው ውድ መስዋትነት ፍሬ እራስን በእራስ የማስተዳደር መብቱን በህዳር 10/2012 ዓ.ም በተካሄደው እና ከ2.3 ሚልዮን በላይ መራጮች ተሳትፈውበት ከ98/100 በላይ ይሁንታን በሰጡበት ህዝበ-ውሳኔ አማካኝነት በድል ማጠናቀቁ ይታወቃል። ምንም እንኳን ለዚህ ጣፋጭ ድል ለመብቃት ያሳለፈነው ጉዞ እጅግ መራራ ቢሆንም ክብር እና ምስጋና በትግሉ ወቅት ለተሰዉ ታጋይ ሰማዕታት ይሁንና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን የአደራ እዳ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቋጭ አድርገናል።
በህዝቡ ህገመንግስታዊ ጥያቄ እና ህገመንግስቱን ተከትሎ ጥያቄውን ለማስመለስ ሲያካሂድ በነበረው ሰላማዊ የትግል አካሄድ ላይ በመንግስት በኩል በተፈጸመ ኢ-ህገመንግስታዊ የፖለቲካዊ ደባ ምክንያት ከ140 የሚልቁ ንጽሀን የሲዳማ ተወላጆች ህይወት መቀጠፉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። "ለህገመንግስታዊ ጥያቄያችን ህገመንግስታዊ ምላሽ ብቻ እናሻለን" በሚል መርህ ሲካሄድ በነበረው ሰላማዊ ትግል ወቅት ላይ ከህገመንግስቱ ድንጋጌ እና አካሄድ ውጪ በሆነ መልኩ ከመንግስት በኩል የቀረቡ አማራጭ የፖለቲካ ውሳኔዎችን አምርረን መቃወማችን ይታወሳል።
ይሁንና ህዝቡ ባደረገው ተቃውሞ እና በከፈለው መስዋትነት የብሄሩ እራስን በእራስ የማስተዳደር ጥያቄ ህገመንግስቱ በምያዘው መልኩ ከሁለት ወራት በፊት በተካሄደው ህዝበ-ውሳኔ ክልል ለመሆን የሚያስችለንን ድምጽ በማግኘት ያጠናቀቅን ቢሆንም የህዝበ-ውሳኔው ውጤት ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ በደቡብ ክልል መንግስት እና በሲዳማ ክልል መካከል መደረግ የነበረበት የስልጣን ርክክብ ሳይካሄድ ቆይቷል።ህዝቡ ይህን የመንግስት ዝግመታዊ የሴራ አካሄድ በጥርጣሬ በመመልከት ባስቸኳይ የስልጣን ርክክቡ እንዲካሄድ በሲዳማ ተወካዮች ላይ እና በሚመለከተው አካል ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድር የከረመ ሲሆን እስከ ጥር 30 ድረስ የስልጣን እርክክቡ ተጠናቆ የክልል ምስረታ ስነ-ስርዓት እንደሚደረግ የተገባለትን ቃል በታላቅ ጉጉት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
ከዚህ ውሳኔ ውጪ አሁን በተለያዩ አካላት በኩል የሲዳማን ህዝብ እራስን በእራስ የማስተዳደር መብት ለመጋፋት እና በህገመንግስቱ መሰረት ምላሽ አግኝቶ የተቋጨን ጥያቄ በፖለቲካ ውሳኔ ወደ ኋላ ለመቀልበስ የሚደረጉ ሙከራዎች ሁሉ ካለፉ ስህተቶች ያለመማር እና አሁንም አላስፈላጊ የህዝብ ደም ለማፍሰስ የሚደረግ አደገኛ አካሄድ እንደሆነ አድርገን እንወስደዋለን፡፡የሲዳማን ህዝብ የዘመናት ጥያቄ ለማስመለስ ቆርጦ የተነሳው ይህ የመጨረሻው ትውልድ(ኤጄቶ) እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ አሁንም መርህ አልባ የሆኑ ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን በጽናት የሚታገል መሆኑንና በደም የተገኘውን የህዝባችንን ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነት ለድርድር የማያቀርብ መሆኑን ሁሉም ጠንቅቆ እንዲገነዝብ እንፈልጋለን።
Comments
Post a Comment