የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምስረታ በአጭር ጊዜ ውስጥ አውን ማድረግ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ለምዕተ አመትና ከዚያ በላይ የሲዳማ ብሔር ለመብቱ እና ነጻነቱ የህይወት እና አካላዊ መስዋዕትነትን በመክፈል ትግል ማድረጉ የሚታወቅ ነው፡፡
በዚህም ጥቂት የማይባሉ የብሔሩ ተወላጆች ከአጼው ዘመን ጀምሮ እስከ ኢህአዲግ አገዛዝ ድረስ በተደራጀ እና ባልተደራጀ መልኩ ኢፍትሀዊነትን እና አንባገነንነትን በመታገል ጭምር የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ችለዋል፡፡
ይህ ከሀገር አልፎ በጎረቤት ሀገር ሞቃዲሾ ሳይቀር ወታደራዊ ትግልን በተደራጀ መልኩ በማድረግ ጭምር አስፈላጊውን የነጻነት ታጋዮችን በማጠናከር ትግሉን ያለማቋርጥ ያደረገው የሲዳማ ብሔር ዛሬ ላይ የታየውን ድል ለመጎናጸፍ ያላሰለሰ ጥረቱ ሆኖም ይገኛል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም የብሔሩ ምሁራን እና አክቲቪስቶች በተመሳሳይ መልኩ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የፖለቲካዊ የዲፕሎማሲ አማራጮችንም ሆነ ነጻ የሆኑ ትግሎችን በማቀጣጠል የበኩላቸውን መወጣት ችለዋል፡፡
በዚህ አይነት መልኩ ከዳር ይደርስ ዘንድ ዋጋ የተከፈለበት ይህ የብሔራችን ትግል በርካቶች መስዋዕት የሆኑበት እና በርካቶች ደግሞ አካላዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ ማቅ እስከመልበስ ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉበት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ለሀገራችን ጭምር አዲስ የትግል እሳቤን በማከል እንዲሁም ለህብረ ብሔራዊ ፌድራላዊ ስርዓታችን መጎልበት አዲስ ምዕራፍ እስከመሆን በደረሰ መልኩ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ነጻ፣ ፍትሀዊ እና ሁሉን አቀፍ የሆነ ህዝበ ውሳኔን ማረጋገጥ ያስቻለ ምርጫ ማካሄዳችን ይታወቃል፡፡
በዚህም መላው የሀገራችን ህዝቦች፣ ታላላቅ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት ሚዲያዎች ሳይቀሩ በግልጽ እውቅና የቸሩት የምርጫ ሂደት እና ውጤትን እውን ማድረግ ያስቻለ ጨዋ አሰራር እና ከጨዋ ህዝብ እና ማንነት የሚጠበቅ ተግባርን እውን ማድረግ ችለናል፡፡
ይህን ተከትሎ ግን ላለፈው አንድ ወር የብሔራዊ ክልላችንን ምስረታ በይፋ እውን መሆን አንዳንድ የውስጥ እና የውጭ አሰራሮችን ከማስተካከል አንጻር መጓተቶች መኖራቸውን ተከትሎ በብዙዎቻችሁ ዘንድ ጥያቄ እየሆነ ሲንጸባረቅም ማየት ችለናል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በይፋ 10ኛው ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም ሆኖ የሲዳማን ብሔር በፌድራላዊ መዋቅራችን አንዱ ማንነት በመሆን እውን የሚያደርገው አደረጃጀትን አስመልክቶ ከደቡብ ክልል ጋር አስፈላጊውን ሁሉ በማከናወን እና ለዚሁ ስኬት አስፈላጊ የሆኑ የኮሚቴ መማክርቶችን በማዋቀር ተገቢው እንቅስቃሴ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ይህ በተለያየ ዘርፍ እና ተልዕኮ ተዋቅሮ ለክልላዊ አደረጃጀቱ ይፋ መሆን እየተንቀሳቀሰ ያለው የኮሚቴ መማክርት አሁን ባለው ፍጥነት እና ትጋት በአጭር ጊዜ ውስጥ በተጨባጭ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን በርክክቡ እውን የሚያደርግ እንደሚሆን ይታመናል፡፡
ይህ በብርቱ የሲዳማ ልጆች ትግል እና በለውጡ መሪ ምላሽ ያገኘው የዘመናት ጥያቄ ትግሉን የሚመጥን ዝግጅት ስለምፈልግ በእለቱም ከሀር ውስጥ እና ከባህር ማዶ ታላላቅ የሀገር መሪዎች፣ ዲፖሎማቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች እና ምሁራን እንደሚገኙ ያለው መርሀ ግብር ያስረዳል፡፡
በመሆኑም መላው ህዝባችን በተደራጀ መልኩ ለክልሉ ምስረታ ይፋ መሆን እየተከናወነ ያለውን ተግባር እና ተልዕኮ በመገንዘብ ከመወዲሁ ዝግጁ በመሆን ክልላችንን በጋራ እንመስርት ለማለት እንወዳለን፡፡
ምንጭ፤ የከተማዋው አስተዳደር ነው
- Get link
- Other Apps
Comments
Post a Comment