ሲአን በሲዳማ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በአገሪቱ ባለው የፖለቲካ ተሳትፎ ረዥም እድሜ ካስቆጠሩ አንጋፋ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። ድርጅቱ ላለፉት ከ 40+ አመታት የሲዳማን ህዝብ ፖለቲካዊ እና ዴሞክራሲያዊ ጥቅሞችን በማስቀደም ስሰራ ቆይቷል። ለዚህም በከፈለው ከፍተኛ መስዋእትነት ለሲዳማ ህዝብ ያጎናጸፋቸው በርካታ ድሎች በህዝቡ የታሪክ ማህደራት በኩራት ተመዝግበው ይገኛሉ።
ሌላው ቀርቶ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ብቻ፣ የሲዳማ ህዝብ የራሱን ክልላዊ መስተዳድር ዳግም ለማዋቀር በሚያደርገው ትግል ከየትኛውን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት በበለጠ ፤ ከህዝቡ ጎን በመቆም እና የህዝቡን ድምጽ በማሰማት እኩሪ ተግባራትን አከናውኗል።
ሲአን ለሲዳማ ህዝብ ከሰራው አኩር ተግባር የተነሳ ብቻ ሳይሆን፤ የሲዳማ ህዝብ በተለይ በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ ባለው የክልሉ ገዥ ፓርቲ የሚደርስበት የማግለል እና ጸረ ሲዳማ አካሄድ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሲአንን በሁለት እግር መቆም አንገብጋቢ አድርጎታል። የሲዳማ ህዝብ በማካሄድ ላይ ያለውን ፖለቲካዊ ትግል ከዳር ለማድረስ መሪ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን፤ መሪ ድርጅትም ያስፈልገዋል። አሁን ባለው ሁኔታ የሲዳማን ትግል በመምራት ከፍተኛ ሚና ሲጫውቱ የነበሩ ኤጄቶች በየእስር ቤቶች በመማቀቅ ላይ በመሆናቸው፤ እንደህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነቱ የህዝቡን ትግል ለማስቀጠል፤ የሲዳማ ህዝብ የሲአንን መጠንከር ከምንም በላይ ይፈልገዋል።
ታዲያ በዚህ አንገብጋብ ወቅት ሲአንን አጠንክሮ ከመምራት ይልቅ፤ በተለይ አመራሮቹ ለፓርቲ ስልጣን ስሻኮቱ ይታያል። በሁለት ጎራ ተከፍለው በህጋዊነት ዙሪያ የሚጣሉት እነዚሁ አመራሮች፤ ያላቸውን ልዩነቶች ወደ ጎን ትተው የህዝቡን ፖለቲካዊ ጥቅም፤ ከማስቀደም ይልቅ ለራስ ህጋዊነት ስከራከሩ ተሰምቷል።
የሲዳማ ህዝብ በአፊኒ ባህሉ መሰረት መሰል ልዩነቶችን በስከኔ መልኩ፤ በሽማግሌ ፊት መፍታት እንደሚችል አመራሮቹ እያወቁ፤ ለራሳቸውም ሆነ ለሲዳማ ህዝብ ክብር በሌለው መልኩ፤ አደባባይ ወጥተው የህዝብ መሳቂያ እና መሳለቂያ እየሆኑ ይገኛል። ለሲዳማ ሽማግሌዎች ሳይሆን፤ ለአለም አቀፍ የህዝብ መገናኛ አውታሮች ያሉባቸውን ችግሮች ስዘረግፉ ታይተዋል። በጣም የሚያሳፍረው ደግሞ፤ ጸረ ሲዳማ በሆነው የደቡብ ሬድዮ እና ቴሌቭዥን ድርጅት ቀርበው ውስጠ ገበናቸውን መዘርገፋቸው፤ ለሲዳማ ህዝብ ጥሩ የማይመኙትን አካላት ሆድ ያረስ ሆኗል።
ይህ ወቅት የሲአን አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ መላው ሲዳማ በተግባሩም ሆነ በቃሉ አንድ መሆን ያለበት ጊዜ ነው። ስለሆነም ጥለኛ አመራሮቹ የህዝቡን ፖለቲካዊ ጥቅም በማስቀደም ብሎም፤ የድርጅታቸውን የወደፊት ህልውና ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ለአንድ አላማ ብታገሉ መልካም ነው።
Comments
Post a Comment