Skip to main content

የሲዳማ ክልል ምስረታ ህደት እንደምባለው ለድርድር የሚቀርብ አይደለምአንዳንዶች በሲዳማ ክልል ምስረታ ህደት ላይ፤ የክልል ጥያቄው ለድርድር መቅረብ አለበት ስሉ እየተደመጡ ነው። እኛ ግን ህገ መንግስቱን ተከትለን ያቀረብነው ጥያቄ ስለሆነ፣ ህገ መንግስቱ በራሱ ለድርድር ካልቀረበ በስተቀር ፤ የክልል ጥያቄያችንን ለድርድር የሚናቅርብበት ምንም ምክንያት የለም። ለማንኛውን የዚህ ሳምንቱ የክልል ጥያቄያችሁን ለድርድር አቅርቡ ባይ አመለካከት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በዚህ መልኩ ስፍሯል።   

ድርድር ግድ የሚለው የክልልነት ጥያቄ
በዮናታን ተስፋዬ ፍስሐና በቢኒያም መንበረወርቅ
ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ከፍ ያለ የሕዝብ ብዛት ካላቸው ብሔረሰቦች መካከል አንዱ የሆነው የሲዳማ ማኅበረሰብ ያቀረበው የክልልነት ጥያቄ በአንድ ዓመት ውስጥ ምላሽ ሳያገኝ መቅረቱን ተከትሎ፣ የራሱን ክልል በራሱ ፈቃድ ብቻ ለማወጅ እንደተዘጋጀ የሚገልጹ መረጃዎች እየወጡ ነበር፡፡ ‹‹11/11/11›› ተብሎ ተደጋግሞ የተጠቀሰው ቀን የአዲስ ክልል ምሥረታውን ለማወጅ በተዘጋጁት በታላቅ ተስፋ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን፣ በአንፃሩ በሁኔታው ሥጋት የገባቸው በርካቶች ደግሞ የዞኑ ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ የሲዳማ የክልልነትን ጥያቄ ያቀረበበትን ቀን መሠረት ተደርጎ የተሰላው የአንድ ዓመት ቀጠሮን፣ ሌላ የደም መፋሰስ ምክንያት እንዳይሆን በፍርኃት ነበር የጠበቁት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሳምንታት በፊት የሰጡት ማስጠንቀቂያ፣ የሲዳማ ዞንና የደቡብ ክልልን በገዥ ፓርቲነት የሚመራው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከበርካታ ቀናት ውይይት በኋላ ያወጣው መግለጫ፣ በአዲስ መልክ የተዋቀረው ምርጫ ቦርድ በአምስት ወራት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔውን ለማከናወን ቃል መግባት ሁሉ የተፈራውን ሊያስቀረው አልቻለም፡፡ እንደ ሞት ቀጠሮ በተፈራው ቀን ሐዋሳ አንፃራዊ መረጋጋት ኖሯት ብታሳልፍም፣ በሲዳማ ዞን ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ከተሞች ግን ለተከታታይ ጥቂት ቀናት የቀጠለ ብሔር ተኮር ጥቃትና ግርግርን አስተናግደዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም ከክልሉ መንግሥት ቀረበልኝ ባለው ጥያቄ መሠረት የፌዴራሉ መንግሥት የደቡብ ክልልን ፀጥታ የማስከበር ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ማዋሉ በመገናኛ ብዙኃን ይፋ ሆኗል (እዚህ ላይ እስካሁን ባለው የፌዴራል ሥርዓቱ ዕድገት ክልሎች በምን ዓይነት አግባብና የትኛውን የመንግሥት መዋቅር ተጠቅመው የፌዴራሉ መንግሥቱን ጣልቃ ገብነት እንደሚጠይቁ በግልጽ የሚታወቅ አሠራር እንደሌለ ልብ ይሏል)፡፡ መሠረታዊው ጥያቄ ባይመለስም ክልሉ ግን ቢያንስ ለጊዜውም ቢሆን፣ የተሻለ መረጋጋት ላይ የሚገኝ መስሏል፡፡
የክልልነት ጥያቄ
በአገሪቱ ከሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል በሕዝብ ብዛቱ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሲዳማ ማኅበረሰብ፣ በደቡብ ክልል ውስጥ ከሚገኙ 60 ገደማ ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ግን ሁሌም የነበረ አይደለም፡፡ ከአፄዎች ጊዜ ጀምሮ ሲዳማ ከማኅበረሰቡ ስያሜ ጋር የተያያዘ አስተዳደራዊ አሀድ የማዋቀር ታሪክ እንደነበረው ዕሙን ነው፡፡ የቅርብ ጊዜውን ታሪክ ብናይ እንኳ ሲዳማ ወሳኝ ብዙኃን ቁጥሩን የያዘበት ክልል የሽግግር መንግሥቱን ከመሠረቱት ክልሎች መካከል አንዱ ሆኖ ተቋቁሞ ነበር፡፡ ይሁንና ይህ የክልል መዋቅር የሽግግር ጊዜውን ዕድሜ ያህል ብቻ ነበር፡፡ አሁን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ተብሎ የሚጠራው ክልል የተወለደው ሲዳማ የነበረበትን ክልል ጨምሮ፣ ሌሎች ተመሳሳይ አራት ክልሎችን ወደ አንድ ክልልነት በመቀላቀል ነው፡፡
ውህደቱ ከተፈጸመ ጊዜ ጀምሮ የሲዳማ ማኅበረሰብ በተደራጀና ባልተደራጀ መንገድ ክልል የመሆን ጥያቄ ማንሳቱን አላቆመም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ ማንሳት ጥርስ በሚያስነክስበት ወቅት እንኳ፣ የማኅበረሰቡ አባላት አቤቱታቸውን በግልጽ ለፌዴራል መንግሥቱ ለማቅረብ የደፈሩበት እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡  የፓርቲ አባላት ለገዥው ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔዎች በጥብቅ እንዲታዘዙ ለሚያደርገው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተብሎ በሚታወቀው መርህ ምክንያት፣ በዞን ምክር ቤት ሳይቀር በሙሉ ድምፅ አስወስነው ያቀረቡትን ጥያቄ የሚሽር ደብዳቤ ራሳቸው በመጻፍ መሻታቸው ሕገ መንግሥታዊውን ሥነ ሥርዓት ተከትሎ ተግባራዊ ውጤት ሳያመጣ በአጭር ተቀጭቷል፡፡
ይህ ከሆነበት ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ብዙ ነገር ተቀይሯል፡፡ በተለይም ዓብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ሲመረጥና አዳዲስ የፖለቲካ ማሻሻያዎችን ሲያስተዋውቅ፣ የሲዳማ ማኅበረሰብ ልሂቃን ነባር ጥያቄያቸውን ዳግም ለማንሳት አዲስ የዕድል በር እንደተከፈተላቸው ሳይታዘቡ አልቀሩም፡፡ በዚህ ላይም የፌዴራል መንግሥቱን ውሳኔዎች በክልል መንግሥታት በጥብቅ የሚያስፈጽመው የፓርቲ መዋቅር በቀደመው ጥንካሬ ላይ አለመገኘቱም በግልጽ የሚታይ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህ ሁኔታም የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ተደፋፍሮ ከደቡብ ክልል የመነጠል ፍላጎቱን በአደባባይ እንዲገልጽና ሕዝበ ውሳኔውም እንዲደራጅለት እንዲጠይቅ እንደገፋፋው መታዘብ ይቻላል፡፡ ለብዙዎች መደነቅን በፈጠረ ሁኔታ የደቡብ ክልል ምክር ቤትም የክልሉ ገዥ ፓርቲ በጉባዔው አስቀምጦታል ያለውን አቅጣጫ መሠረት አድርጎ፣ የሲዳማ የሕዝበ ውሳኔ ጥያቄን በመቀበል የሲዳማ  ሕዝብ ዕጣ ፋንታው ላይ እንዲወስን ጉዳዩን ወደ ምርጫ ቦርድ መራው፡፡ በዚህ አዲስ ተስፋ የተነቃቁት የሲዳማ ማኅበረሰብ አባላትም፣ ለክልልነት ጥያቄያው ያላቸውን ድጋፍ በተለያየ መንገድ በመግለጽ አሳዩ፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ የሲዳማ እናቶችና ወጣቶች በዓይነቱ ልዩ በሆነው የሴቶች ብቻ ሠልፍ ላይ በመታደም፣ ከደቡብ ክልል ለመነጠሉ ሐሳብ ያላቸውን ድጋፍ ያሳዩበት ሁኔታም በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ልዩ ሁነት ነበር፡፡ 11/11/11 ሲቃረብም የሲዳማ ክልል ባንዲራ ይሆናል የተባለ ዓርማ በሐዋሳና አካባቢዋ በሰፊው መታየቱና ‹‹እንኳን ወደ ሲዳማ ክልል በሰላም መጣችሁ፤›› የሚል የጎዳና ዳር ማስታወቂያ መሰቀሉ፣ የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳታፊዎችን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ አዲስ የሚመሠረተው ክልል ረቂቅ ሕገ መንግሥት ላይም ምክክሮች መካሄድ መጀመራቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች መውጣታቸው፣ በአንድ ወገን ውሳኔ ክልል ምሥረታውን ለማከናወን የተያዘው አቋም ጥንካሬን የሚያሳብቅ ነበር፡፡ ታዋቂ የሲዳማ ሕዝብ መብት አንቂዎችም መንግሥት ከተባለው የቀን ቀጠሮ በፊት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ፣ ይህ ካልሆነ ግን የሲዳማ ክልል ምሥረታን በማወጅ ሐሳባቸው እንደሚገፉበት አስጠነቀቁ፡፡
የክልልነት ጥያቄን የሚያበረታ ፌዴራሊዝም?
ከሰማንያ የማያንሱ ብሔረሰቦችን አቅፋ የያዘችው ኢትዮጵያ የቀረፀችው ሕገ መንግሥት ፌዴሬሽኑን ያደራጀው፣ ብሔረሰባዊ ማንነትን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ ይሁንና ከዘጠኙ ክልሎች መካከል በወሳኝነት እጅግ በርከት ያለውን ቁጥር ከሚይዘው ማኅበረሰብ ጋር ተያይዘው የተደራጁት ክልሎች አምስት ብቻ ናቸው፡፡ የተቀሩት ግን አንድ ማኅበረሰብ ከሃምሳ በመቶ በላይ የሚሆነውን የሕዝብ ብዛት የማይዝባቸው በማያጠያይቅ ሁኔታ ብሔረ ብዙ ሆነው ነው የምናገኛቸው፡፡ በውጤቱም ጥቂት ብሔረሰቦች ብቻ ‹‹የራሳቸው›› ክልል ሲኖራቸው ሌሎች ብዙዎች ግን ይህንን ዕድል ለማግኘት አልታደሉም ማለት ነው፡፡ ይህን ሁኔታ ይበልጥ የሚያወሳስበው እውነታ ደግሞ በሕዝብ ቁጥራቸው ትልልቅ የሆኑ ብሔረሰቦች ክልል መሆን ተነፍጓቸው፣ በቁጥራቸው እጅግ ትንሽ የሆኑ ብሔረሰቦች በስማቸው የሚጠራ ክልል ‹‹ባለቤት›› እንዲሆኑ የተፈቀደበት አያዎ (Pardox) ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተደጋግሞ የሚነሳው በጥቂት ሺሕዎች የሚቆጠር ሕዝብ ነዋሪ ያለው የሐረሪ ሕዝብ በስሙ የሚጠራ ክልል  እንዲኖረው መደረጉ፣ በአንፃሩ ሲዳማን የመሰሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ያላቸው ሌሎች ማኅበረሰቦች ግን ‹‹የራሳቸው›› ክልል ሳያገኙ መቅረታቸው ነው፡፡ በእርግጥም የሲዳማ ማኅበረሰብ የሕዝብ ብዛት ከተወሰኑት ክልሎች የሕዝብ ብዛት ድምር የላቀ ቁጥር ነው ያለው፡፡
ከሞላ ጎደል ሳይደበዝዝ ለዘመናት የዘለቀው የሲዳማ የክልልነት ጥያቄም በከፊል ቢሆን ከላይ በተጠቀሰው ወጥነት በጎደለው አሠራር ምክንያት የተበረታታ ነው ማለት ስህተት አይሆንም፡፡ ክልል በመሆን ከሚገኝ ትእምርታዊ (Symbolic) ጥቅም ባሻገርም፣ ‹‹የራሳቸው›› ክልል ያላቸው ብሔረሰቦች በሕገ መንግሥቱ እንደ ቅደም ተከተላቸው ለክልሎችና ለብሔረሰቦች የተሰጡ ሥልጣንና ኃላፊነቶችን ጠቅልለው ሲወስዱ፣ በክልል ደረጃ ያልተዋቀሩ ብሔረሰቦች ግን ለክልሎች የተሰጡ ሥልጣንና ኃላፊነቶች በቀጥታ አይመለከታቸውም፡፡ ለምሳሌ በክልል ደረጃ ያልተዋቀሩ ማኅበረሰቦች ከሌሎች መካከል በሕገ መንግሥት ማሻሻያ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ የላቸውም፡፡ በእርግጥ ሲዳማን የመሰሉ አንዳንድ ብሔረሰቦች በዞን ደረጃ የተዋቀረ አደረጃጀት ኖሯቸው በየክልሉ ሕግጋተ መንግሥታት ለብሔረሰብ ዞኖች የተሰጡ ሥልጣኖች ባለቤት ናቸው፡፡ ሰፊ የቋንቋና የባህል መብቶችም በዞን ደረጃ ተግባራዊ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን እነዚህ ለአውራጃ መንግሥታት የተሰጡ ሥልጣንና ኃላፊነቶች በክልል ደረጃ ከሚገኙት ጋር በፍጹም የሚወዳደሩ ሆነው አናገኛቸውም፡፡ በቀጥታም ባይሆን ብሔረሰቦች በፌዴራል ሥርዓቱ አስተዳደራዊ አወቃቀር ተዋረድ የሚገኙበት ቦታ፣ ከፌዴራል መንግሥቱ የሚያገኙትን የገንዘብ መጠን የመወሰኑ ጉዳይ ከዚህ አኳያ በጉልህ የሚነሳ ነጥብ ነው፡፡
በክልል ደረጃ የተዋቀሩ ማኅበረሰቦች ከገቢያቸው ዳጎስ ያለውን ክፍል የሚይዘውን የፌዴራል ድጎማ በቀጥታ የሚያገኙ ሲሆን፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ የተደራጁት ግን የፌዴራል ድጎማውን የሚያገኙት ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በክልል ደረጃ በሚደረግ ሁለተኛ ድልድል ነው፡፡ ይህን ተከትሎም በቀጥታ ከፌዴራል መንግሥት የድጎማ በጀት የማይሰፈርላቸው ራሳቸውን በአውራጃ መንግሥት ደረጃ የሚያስተዳድሩ ብሔረሰቦች ዓመታዊ በጀት፣ የራሳቸው ክልል ካላቸው ተቀራራቢ የሕዝብ ቁጥር ካላቸው ብሔረሰቦች አንፃር ሲታይ ትርጉም ባለው ደረጃ ያነሰ ሆኖ የሚገኝበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም (ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ) የራሳቸው ክልል ያላቸው ብሔረሰቦች በአንፃራዊነት የሕዝባቸውን ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና፣ ፖለቲካ ሥልጣንና ማኅበራዊ ተቀባይነትን በማረጋገጥ ረገድ እጅግ በተሻለ ቁመና ላይ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው የሐረሪ ሕዝብ ክልል የሚያስጎመጅ ሁኔታ ላይ እንዳለች ሆና በሌሎች ክልል ባላገኙ ማኅበረሰቦች እንድትታይ የሆነችው፡፡ የሲዳማ ብሔርተኞችም ክልልነት ይገባናል የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ እንደ ሐረሪ ሕዝብ ዓይነት ክልሎች ያገኙትን ዕድል እያጣቀሱ መሆኑ የሚጠበቅ ነው፡፡ 
አዲስ ክልል ምሥረታ
አዲስ ክልል ለመመሥረት ለተነሳሱት ሲዳማዎችና ሌሎች ብሔረሰቦች መልካሙ አጋጣሚ፣ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሰል ጥያቄ ለሚያነሱ ብሔረሰቦች የክልልነትን በር ገርበብ አድርጎ ከፍቶ የሚጠብቅ መሆኑ ነው፡፡ የአዲስ ክልል ምሥረታን እንደ ብሔረሰቦች ሕገ መንግሥታዊ መብት ዕውቅና በመስጠትና ይህም የሚፈጸምበትን ዝርዝር ሥነ ሥርዓት በማስቀመጥ ረገድ፣ ምናልባትም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ‹‹አንድ ለእናቱ›› ሆኖ የሚጠቀስ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በእርግጥ አዳዲስ ክልሎችን የፈጠሩና ነባሮችንም ያዋሀዱ ሌሎች ፌዴሬሽኖች መኖራቸው የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ እነሱ ይህን ያደረጉት ግን በጉዳዩ ዙሪያ የፖለቲካ መነሳሳት መኖሩን በተከተለና ይህን ዓይነቱን ሐሳብ ለመቀበል በሚያመነታ የፌዴራል መንግሥት ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የአዲስ ክልል ምሥረታ ጥያቄን ወደ ሕገ መንግሥታዊ መብትነት ከፍ በማድረጉ ምክንያት ከአቻዎቹ ሕግጋተ መንግሥታት የሚለይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47/2 ከክልል ባነሰ ደረጃ ራሳቸውን በማስተዳደር ላይ የሚገኙ ብሔረሰቦች በፈቀዱ ጊዜ፣ የራሳቸውን ክልል የመመሥረት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ መብቱ የሚተገበርበት ሥነ ሥርዓትንም አበጅቷል፡፡ እውነቱን ለመናገር በሕገ መንግሥቱ የተዘረጋው አዲስ ክልል የሚጠየቅበትና የሚመሠረትበት ሒደት ውጣ ውረድ የሚያበዛ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም፡፡
አንቀጽ 47/3/ እንዳስቀመጠው አንድ ብሔረሰብ ከነበረበት ክልል ተነጥሎ አዲስ ክልል ለመመሥረት ከፈለገ መጀመርያ ጥያቄው በብሔረሰቡ ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ ድጋፍ አግኝቶ፣ በጽሑፍ አባል ለሆነበት ክልል ምክር ቤት መቅረብ ይኖርበታል፡፡ በዚህ አግባብ ጥያቄው የደረሰው የክልሉ ምክር ቤትም በአንድ ዓመት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ያደራጃል፡፡ የክልልነት ጥያቄው በሕዝበ ውሳኔው ከሃምሳ በመቶ በላይ ድጋፍ ሲያገኝና ነባሩ ክልል ሥልጣኑን ለዕጩው ክልል በሚያስተላልፍበት ወቅት፣ በሕዝበ ውሳኔው የተፈጠረው አዲሱ ክልል የፌዴሬሽኑ አባል ለመሆን ማመልከት ሳያስፈልገው በቀጥታ የፌዴሬሽኑ አባል ይሆናል፡፡ ጠቅለል አድርገን ስናየው ክልል ለመመሥረት ጥያቄ ካቀረበው ብሔረሰብ የሚጠበቀው ዋና ነገር፣ ለቀረበው ጥያቄ በቂ የሕዝብ ድጋፍ መኖሩን ማሳየት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው ሃምሳ በመቶ ድጋፍ ማግኘትም ከባድ የሚባል ዓይነት አይደለም፡፡ በአንፃራዊነት ልል የሆነ አዲስ ክልል የመመሥረቻ ሥነ ሥርዓት በመኖሩ የተነሳም ሁሌም እንደ ሥጋት ሲታይ የነበረው ጉዳይ፣ አንድ ማኅበረሰብ ክልል እንዲሆን መፍቀድ ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንዲጎርፉ መንገድ መክፈት ይሆናል የሚለው ነበር፡፡ የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሲዳማ ጥያቄ ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ለምርጫ ቦርድ የጻፈው ደብዳቤ ቀለም ሳይደርቅ፣ ወደ አሥር ገደማ ማኅበረሰቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ ‹‹ክልል ይገባናል›› ብለው መጠየቃቸው የተጠቀሰው ሥጋት መሠረተ ቢስ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ለመመለስ ፍላጎት አሳይቶ የነበረው የደቡብ ክልል ውሳኔውን መልሶ ወደ መመርመርና ጥናት ወደ ማስጠናት የገባው፡፡ የክልልነት ጥያቄም እንደ ሥጋት የሚታይ ተግዳሮት ሆኖ መቅረብ ጀምሯል፡፡
የክልልነት ጥያቄ እንደ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ
ከሳምንታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለፓርላማ አባላት ያቀረቡት ሪፖርትን ተከትሎ በነበረው የጥያቄና መልስ ክፍለ ጊዜ ላይ፣ የክልልነት ጥያቄ ቀደም ሲል ከቀረበው ሒደት ባሻገር የሌሎች ክልሎችም ድጋፍ ያስፈልገዋል ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በሕገ መንግሥቱ የተጠቀሱት ዘጠኝ ክልሎች በመሆናቸውና አዲሱ ክልል አሥረኛ ሆኖ መካተት እንደሚገባው በማንሳት ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር ሲዳማ የፌዴሬሽኑ አባል ክልል ሆኖ በዝርዝሩ ግርጌ ላይ እንዲካተት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ያስፈልጋል፡፡ በውጤቱም የአዲስ ክልል ምሥረታ ጉዳይ ቀደም ሲል ከተጠቀሰው ሒደት ባሻገር የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይም ነው እንደ ማለት ነው፡፡ ብዙ ታዛቢዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ክርክር እንደ ሰማን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸውን ‹‹በድጡና በማጡ›› መካከል ካገኙበት ሁኔታ ለመውጣት በብልጣ ብልጥ የሕግ አተረጓጎም ተግባር (aact of Legal Gymnastics) እንደተሰማሩ አድርገን ለማጣጣል ጊዜ አልወሰደብንም ነበር፡፡ የዚህ መደምደሚያ መነሻ አዲስ የተመሠረተው ክልል ማመልከቻ ማቅረብ ሳያስፈልገው፣ በቀጥታ የፌዴሬሽኑ አባል ይሆናል የሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ነው፡፡  በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልተሳሳቱም ነበር፡፡ ዝቅ ብሎ በዝርዝር እንደሚቀርበው የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ በሁሉም ሒደቶች አልፎ መቋጫ የሚያገኘው፣ ዕጩው ክልል በሕገ መንግሥቱ የፌዴሬሽኑ አባላት ዝርዝር ውስጥ ሲካተት ብቻ ነው፡፡
የ1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱ በአንድ በኩል ሁሉንም የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች በስም ጠቅሶ የሚዘረዝርና በቀላሉ የማይሻሻል አንቀጽ ማካተቱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሌሎች ክልሎች በጎ ፈቃድ ሳያስፈልግ አዲስ ክልል የሚመሠረትበትና በቀጥታም አባል የሚሆንበት ሁኔታን መደንገጉ ተቃርኖን ያዘለ ነው፡፡ ምናልባትም ጉዳዩን አርቃቂዎቹ የፈጠሩት ያልታሰበ ግድፈት አድርገን በማየት የአዲስ ክልል ምሥረታን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጋር አቻ የሚያደርገውን ክርክር ወደ ጎን ለመግፋት እንሞክር ይሆናል፡፡ ይህ አካሄድ ግን ከቅርቃሩ የሚያወጣና ችግሩንም የሚፈታ አይሆንም፡፡ የሲዳማ ብሔረሰብ የተሟላ የፌዴሬሽኑ አባልነትን ሊጎናፀፍ የሚችለው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ከተደረገ ብቻ ነው፡፡ ይህ ማሻሻያም የሁለቱ ምክር ቤቶችን የጋራ ስብሰባ ሁለት ሦስተኛ ድጋፍና ከዘጠኙ የፌዴሬሽኑ አባላት የስድስቱ ምክር ቤቶችን ይሁንታን የሚጠይቅ ነው፡፡ 
እዚህ ላይ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የአዲሱ ክልል ወደ ፌዴሬሽኑ አባላት ዝርዝር መካተት የመብቱ ውጤት በመሆኑ፣ ጉዳዩ ከሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጋር ተያይዞ መነሳቱ ተገቢ አይደለም የሚል ክርክር ያነሳሉ፡፡ አዲስ ክልል መመሥረቱ የክልሎችን ዝርዝር የያዘውን አንቀጽ እንደሚቀይረውም ያምናሉ፡፡ ለውጡ የክልልነት ውጤት (Consequence) እንጂ መንስዔ (Cause) ወይም ቅድመ ሁኔታ (Pre-condition) አይደለም ይላሉ፡፡ ይህ ክርክር ግን ብዙም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ የሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያው የመብቱ ውጤት ተደርጎ መወሰዱ፣ የሕገ መንግሥቱ ማሻሻያው በሚመራበት ጥብቅ ሥነ ሥርዓት ላይ ለውጥ አያመጣም፡፡ የአዲሱ ‹‹ክልል›› የዝርዝሩ አካል የመሆኑ አስፈላጊነት ላይ መተማመን ከተደረሰ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሥርዓት ወደ ተደነገገበት አንቀጽ 105 ከመመልከት ውጪ ሌላ ምርጫ የለም፡፡ አሥረኛውን ክልል የማካተት ሒደትም እንዲሁ በቀላሉ በአስፈጻሚው አካል ወይም በፓርላማ ውሳኔ የሚታረም ተራ የቃላት ግድፈት ተደርጎ ሊቀርብ የሚችልበት ዕድል እንደሌለ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶችን ድጋፍ ግድ የሚል ነው፡፡  እንዲህ ዓይነቱ ክርክር ‹‹ማሻሻያ ሊደረግ የሚችለው በሚከተለው አኳኋን ብቻ ነው፤›› በማለት የሚደነግገውን የሕገ መንግሥቱን የማሻሻያ አንቀጽ፣ በሌላ ከሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ጋር ግንኙነት በሌለው አንቀጽ ለማሻሻል መሞከር ነው የሚሆነው፡፡
እዚህ ላይ ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ክርክር የቀረቡትን ሒደታዊ ቅድመ ሁኔታዎች የሚያሟላ (ያሟላ) ብሔረሰብ፣ ሕገ መንግሥት ሳይሻሻልና በሕገ መንግሥታዊው የአባልነት ዝርዝር ውስጥ መካተት ሳያስፈልገው ክልል ሆኖ መቆጠር ይችላል የሚል ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የማያውቀው ‹‹አካል›› እንዴት ክልሎች በሕገ መንግሥቱ ያገኙትን ሥልጣንና ኃላፊነቶች እንዴት ሊተገበር ይችላል? የክልል መንግሥታት እንዲተገብሯቸው የሚጠበቁት አብዛኞቹ ሥልጣንና ተግባራት ክልሉ የፌዴሬሽኑ አባል ሆኖ ዕውቅና ማግኘቱ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ በፌዴሬሽኑ የአባላት ዝርዝር ውስጥ ያልተካተተ እንዲህ ዓይነቱ ‹‹ክልል›› ምንን መሠረት አድርጎ ሕገ መንግሥታዊ የሆኑትን የክልሎች ሥልጣንና ኃላፊነት ‹ይገቡኛል› ብሎ ሊጠይቅ እንደሚችል፣ ምንን ተመርኩዞ በበይነ መንግሥታት ፎረሞች እንደሚሳተፍ፣ የትኛውንስ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ጠቅሶ የፌዴራል መንግሥቱ የበጀት ድጎማ ተጠቃሚ እንደሚሆን ማሳየት ከባድ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፌዴሬሽኑን አባላት የሚዘረዝረው አንቀጽ አስገዳጅ አይደለም ተብሎ የሚቀርበው ክርክር፣ በሕገ መንግሥቱ ዋና ክፍል የተካተቱ አናቅጽት ይቅሩና የሕገ መንግሥት መግቢያ ውስጥ የተካተቱ ዓረፍተ ነገሮች የአስገዳጅነት ባህሪ እየተሰጣቸው ከመጣበት እውነታ ጋር የሚጋጭ ነው፡፡
በተመሳሳይ የአባልነት ዝርዝር መካተት ጉዳይ ሊነሳ የሚገባው ክልልነቱ በይፋ ከታወጀ በኋላ ነው የሚሉ አስተያየቶችም ይቀርባሉ፡፡ ይህ ግን ለችግሩ መፍትሔ የሚያበጅ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ማሻሻያው ዕውን እንዲሆን የሌሎች ድጋፍ የግድ የሚል በመሆኑ ነው፡፡ የሲዳማ ሕዝብ ሕግን ተከትሎ በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ የሚያሳልፈው ብይን በዴሞክራሲያዊ ሒደት የተገለጸ የሕዝቡ መሻት በመሆኑ፣ ከፍ ያለ ክብር ሊሰጠው የተገባ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም የፌዴራል መንግሥቱና ሌሎች የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች የሲዳማ ዞን በሕገ መንግሥቱ የታወቀ ክልል ሆኖ እንዲመሠረት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እንዲያደርጉ ግዴታን ይፈጥራል ብሎ መከራከር ይቻል ይሆናል፡፡ በሌላ አነጋገር የካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩቤክ የአንድ ወገን የመነጠል ሕዝበ ውሳኔ ላይ በሰጠው ብይን የተጠቀሰውን ዝነኛ ሐረግ በመዋስ፣ ‹‹በጉልህ አብላጫ ድጋፍ የተገለጸ የማያወላውል የሲዳማ ሕዝብ የራሱን ክልል የመመሥረትና ከደቡብ ክልል የመነጠል ፍላጎት››ን (‘a Clear Expression of a will by a Clear Majority’) የተቀረው የአገሪቱ ክፍል እንዲያከብርና ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እንዲያደርግ ግዴታ ሊፈጥር ይገባል እንደ ማለት ነው፡፡ ይሁንና በሲዳማ ውሳኔ በብዙ ሁኔታ ጥቅሙ የሚነካውን የደቡብ ክልል የሕገ መንግሥት ማሻሻያውን ደግፎ እንዲመርጥ ማስገደድ ይቻላልን? ለሲዳማ ሕዝብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለተገለጸ መሻት ሊሰጠው የሚገባ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ቢሆንም፣ ይህ ግን የደቡብ ክልል መንግሥትና ሌሎች የሲዳማ ሕዝብን ፍላጎት ያለ ምንም ድርድርና ውይይት እንዲቀበሉ የሚያስገድድ ሊሆን አይችልም፡፡ ምናልባትም ሊፈጥረው የሚችለው ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ቢኖር፣ የደቡብ ክልልና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ላይ ከሲዳማ ሕዝብ ተወካዮች ጋር ለድርድር እንዲቀመጡ ነው፡፡
እዚህ ላይ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ አርባ ሰባትም ግዴታን የሚጥል ዓይነት የቋንቋ አጠቃቀም እንደሌለው ማንሳት ይገባል፡፡ ጥያቄው ለክልል ምክር ቤት በጽሑፍ ሲቀርብ፣ የክልል ምክር ቤት ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፣ ሥልጣን ሲያስረክብ፣ ወዘተ. ከማለት ባሻገር የግዴታ አመልካች ቃላት የሉትም፡፡ ሌላው ቢቀር ከሥነ ሥርዓታዊ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል አንዱ የሆነው ‹‹የክልሉ ምክር ቤት ሥልጣኑን ሲያስረክብ›› (ሥልጣን ማስረከብ በተግባር ምንም ይሁን ምን) የሚለው ጉዳይ በክልል ጠያቂው ብሔረሰብ የአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የማይሟላና ያለ ውይይትና ድርድር የማይታሰብ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ አዲስ ክልል የመመሥረት መብትን ለብሔረሰቦች ከማጎናፀፍና አዲስ ክልል በሚመሠረትበት ወቅት መከተል የሚገባውን ሥነ ሥርዓት ከመዘርዘር ባለፈ፣ አዲሱ ክልል የሚገነጠልበት ክልል የብሔረሰቡን ፈቃድ እንዲያሟላ የሚገደድበት አግባብ አለማመላከቱ የክልል ምሥረታው ሒደት ድርድርን የሚጠይቅ መሆኑን የሚጠቁም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የሐዋሳ ነዋሪዎች ጥቅምና ፍላጎታቸውን ያገናዘበ ሒደት እንዲኖር አቤቱታ ማቅረባቸው መሰማቱም ይህንኑ ሐሳብ የሚያጠናክር ነው፡፡ ይህ አሠራር ሌሎች ፌዴሬሽኖች በዚህ ረገድ ካዳበሩት አሠራር ጋር የተጣጣመና ስምሙ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ የአንድ ማኅበረሰብ ወይም የተወሰነ ግዛት አዲስ ክልል የመመሥረት መሻትን ብቻ መሠረት አድርጎ የክልል ምሥረታን የሚፈቅድ አገር የለም፡፡ ከስዊዘርላንድ እስከ ህንድ ያሉ ልምዶች እንደሚያሳዩት በአዲስ ክልል ምሥረታ ሒደት ውስጥ ማዕከላዊ መንግሥታት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡
ሕገ መንግሥቱ የአዲስ ክልል ምሥረታ ጥያቄ ቀርቦ፣ ነገር ግን ክልሉ ወይም የፌዴራሉ መንግሥት ጥያቄውን ለመቀበል በሚያመነቱበት ወቅት ምን ሊደረግ እንደሚገባ በግልጽ አላመላከተም፡፡ በተጨባጭ ግን ሕገ መንግሥቱ አዲስ ክልል ምሥረታ የሚያልፍበትን ሥነ ሥርዓት ያስቀመጠ ሲሆን፣ ይህ ሥነ ሥርዓትም በአንድ ወገን የራስ ክልል ማወጅን የሚፈቅድ ሆኖ አናገኘውም፡፡ ከዚህም በላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመወሰን የወጣው አዋጅ 251/93 በአንቀጽ 19/3 በማያሻማ ሁኔታ እንዳስቀመጠው፣ የክልልነት ጥያቄ ያቀረበው ማኅበረሰብ የክልል መንግሥቱ በሚገባ አላስተናገደኝም ወይም በሰጠኝ ውሳኔ አልረካሁም ብሎ ባሰበ ወቅት፣ የክልል መፍትሔን አሟጦ ከጨረሰ በኋላ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጉዳዮችን የመከታተል ሥልጣን ወደ ተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታውን እንዲያሰማ ይፈቅዳል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ጉዳዩን መርምሮ የመጨረሻ ብይን ለመስጠት ከሁለት ዓመታት ያልበለጠ ጊዜ ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ድንጋጌ  እንደሚያሳየው የክልልነት ጥያቄ ያቀረበ ማኅበረሰብ ጥያቄዬ በአንድ ዓመት ውስጥ መልስ አላገኘም ብሎ በአንድ ወገን ብቻ የሚደረግ የክልል ምሥረታን ወደ ማወጁ ከማምራቱ በፊት፣ ሊከተላቸው የሚገቡ ቀድመው የተቀመጡ ፍትሕ የማግኛ ሕጋዊ ሥነ ሥርዓቶች መኖራቸውን ነው፡፡ የሲዳማ ማኅበረሰብ አባላት በአንድ ወገን ብቻ የሚደረግ (Unilateral) ክልል የመመሥረት ዕቅድም፣ ሕገ መንግሥታዊ ያልነበረው ከላይ በቀረቡት ምክንያቶች ነው፡፡
ትብብርን መሠረት ያደረገ የአዲስ ክልል ምሥረታ ሒደት
ሁሉም መንገዶች ወደ ባለድርሻ አካላት የጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር የሚያመሩ ይመስላል፡፡ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄም መቀልበስ ወደማይችልበት ደረጃ የደረሰ ይመስላል፡፡ የክልሉና የፌዴራሉ መንግሥት ባለሥልጣናትም ክልል ለመሆን የሚቻልበት ብቸኛ ሕጋዊ ጎዳና ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ መሆኑ ዕውቅና ባገኘበት ማዕቀፍ፣ የሲዳማ ማኅበረሰብ ሕዝበ ውሳኔ የሚያደርግበትን ሁኔታ ከማመቻቸት ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡ ምናልባትም ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር ወደ ድርድር መግባትና እስካሁን በሚገባ ምላሽ ያላገኙትን በሕዝበ ውሳኔው በመምረጥ መሳተፍ የሚችለው ማን ነው? የሀብት ክፍፍል እንዴት ነው የሚከናወነው? ሲዳማ ክልል የሚሆን ከሆነ በዞኑ የሚኖሩ የሌሎች ብሔረሰቦች አባላት መብትና ጥቅማቸው እንዴት ነው የሚከበረው? ለሚሉትና መሰል ጉዳዮች መላ መዘየድ ነው፡፡ አሁን እጅግ የተፍረከረከው የአገሪቱ ፖለቲካ ሁኔታ ከደቡብ ክልል በዘፈቀደ ለመገንጠል የሚደረግ ሙከራና ሌሎችም የሚያደርጉትን ተመሳሳይ ግፊት ተከትሎ የሚከሰት ሁከትን መሸከም የሚችል ትከሻ የለውም፡፡ በተመሳሳይ የፌዴራል መንግሥቱ  ጥያቄዎቹን በጉልበት ወደ መጨፍለቅ የማዘንበል ሙከራ አገሪቱን ወደባሰ የአመፅና የአለመረጋጋት አዘቅት የሚከታት መሆኑን አውቆ ሊያስወግደው ይገባል፡፡ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላትም ትብብርንና ድርድርን መሠረት ያደረገ የአዲስ ክልል ምሥረታ ሒደት እንዲኖር መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ የክልልነት ጥያቄ እንደ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ መታየቱም ይህንኑ ዕድል የሚሰጥ፣ የድርድሩን መንገድ የሚጠቁም አድርጎ መውሰድ ጠቃሚ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ዮናታን ተስፋዬ ፍስሐ (ዶ/ር) በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዌስተርን ኬፕ የሕግና ፌዴራሊዝም ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ቢኒያም መንበረወርቅ ደግሞ በትሬንቶ ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ተማሪ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊዎቹን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊዎቹን እንደ ቅደም ተከተላቸው በኢሜይል አድራሻቸው yfessha@gmail.com እና yambinimw@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Comments

Popular Posts

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

የለበሰው ያደፈ ቁምጣና ሹራብ ከቅዝቃዜው አላዳነውም፡፡ ካፊያው ልብሱን አርሶታል፡፡ ሽው እያለ ከሐይቁ የሚነሳው ነፋስ የሚፈጥረው ቅዝቃዜ ያንቀጠቅጠዋል፡፡ የተጫማው ያረጀ ሲሊፐር እግሩን ከምንም አላዳነውም፡፡ በባዶ እግሩ የሚራመድ ያህል ጨቅይቷል፡፡ ተደባዳቢ ይመስል ፊቱ የተሞነጫጨረ ነው፡፡ ገና 12 ዓመቱ ቢሆንም፣ ቁመናው እንደ ትልቅ ሰው ግዙፍ ነው፡፡ የሚለብሰውን እንደ ልቡ ባያገኝም፣ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ቤሳቢስቲን የሌላቸው ወላጆቹን አያስቸግርም፡፡ ከቤተሰቦቹ ጋር ከሚኖሩበት ታቦር ተራራ ጀርባ ወዳለው ሐዋሳ ሐይቅ ከወረደ እንኳንስ የራሱን የቤተሰቦቹንም የዕለት ጉርስ የሚሸፍንበት ገንዘብ አያጣም፡፡ የአስጎብኚነት ዕውቀት፣ ከሐይቁም ውስጥ ዓሳ የሚያጠምድበት መረብም ሆነ ፈቃድ የለውም፡፡ ሙሉቀን (ስሙ ተቀይሯል) እና ጓደኞቹ ሐይቁን ለመጎብኘት የሚሄዱ ጎብኚዎች በካሜራቸው ጥሩ ፎቶ እንዲያስቀሩ ድባቡን የማሳመር ሥራ ይሠራሉ፡፡ ካሜራውን ይዞ ቁጭ ብድግ እያለ ጥሩ ፎቶ ለማንሳት ጥረት የሚያደርግ ሲያዩ፣ ቆርጠው የያዙትን የዓሳ ሥጋ ይዘው ጠጋ ጠጋ ይላሉ፡፡ ቁርጥራጩን የዓሳ ሥጋ ምግብ ለሚቀሙት አባኮዳዎች ሻሞ ይላሉ፡፡ የተወረወረላቸውን ቀድመው ለመቅለብ አባኮዳዎቹ ክንፋቸውን እየመቱ ወደ ላይ ብድግ ይላሉ፡፡ የናሽናል ጆግሪፊ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ያነሱት ዓይነት ፎቶዎች ሳያስቡት ያነሳሉ፡፡ በሁኔታው ተደስተው ደጋግመው ድንቅ ፎቶዎችን ለመውሰድ ሲዘጋጁ እነ ሙሉቀንም አጀንዳቸውን ይፋ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ አቶ ዳዊት አብርሃም ‹‹አንዱን ዓሳ በአሥር ብር ገዝቼ ነው እንዲህ የማዘጋጀው፤›› በማለት በቅድሚያ  መረጃ ይሰጣሉ፡፡ ለቀጣዩ ዜና በዚህ መልኩ እንዲዘጋጁ ካደረጉ በኋላ፣ ሌሎች ሰዎች መቶም ሁለት መቶም ብር እንደሚሰጧቸው ቀለል

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የመንግሥት ስልጠና የምርጫ ቅስቀሳ አካል ነው ብሏል  የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ለምን ወጣ መባሉ ተገቢ አይደለም - ምርጫ ቦርድ ምርጫ ቦርድ ከኢህአዴግ ተፅዕኖ ሙሉ ለሙሉ ነፃ መሆኑ ሳይረጋገጥና የምርጫ አፈፃፀም ችግሮች ሳይወገዱ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ለማወጅ መዘጋጀቱ ተገቢ አይደለም ሲል ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመሩት ኢማዴ-ደህአፓ ተቃወመ፡፡ መንግስት፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎችን ጨምሮ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየሰጠ ያለው ስልጠና የምርጫ ቅስቀሳ አካል ነው ሲልም ፓርቲው ኮንኗል፡፡  የኢትዮጵያ ማህበረ ዴሞክራሲ ደቡብ ህዝቦች አንድነት ፓርቲ ሰሞኑን ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባስገባው ግልፅ ደብዳቤ፤ ያለፉት አገር አቀፍና የአካባቢ ምርጫዎች ከመካሄዳቸው በፊት በምርጫ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር የሚወያይበት መድረክ እንዲዘጋጅ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም እስካሁን ከቦርዱ የተሰጠ ተግባራዊ ምላሽ የለም ብሏል፡፡  ሃገሪቱ “በአንድ አውራ ፓርቲ” ብቸኛ ቁጥጥር ስር መውደቋ አደገኛና አሳሳቢ ነው ያለው ፓርቲው፤ የመድብለ ፓርቲ ስርአት የመገንባት ተስፋችን ጨርሶ እንዳይከስም ቦርዱ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የሚካሄድበትን ሁኔታ ለመፍጠር ገዥው ፓርቲና ሃቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚወያዩበት መድረክ እንዲያመቻች በህግ ስልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድ የገባውን ቃል በማጠፍ መድረኩን ሳያመቻች የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀቱ ፋይዳ የለውም ብሏል - ፓርቲው፡፡  ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በተሻሻለው የምርጫ ህግ፣ ለቦርዱ የተሰጠውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ የማስተባበር ስልጣን ለመቀማት ታማኝ ፓርቲዎችን በተቃዋሚ ስም አሰባስቦ “የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ” በመፍጠር የምርጫ ውድድር አሯሯጭ አሰልፏል ሲ

የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል ማለፊያ ነጥብ ውጤት ነገ ይፋ ይሆናል

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 23 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) የ10ኛ ክፍል ማጠቃለያና የ12ኛ ክፍል መሰናዶ ማለፊያ ነጥብ ውጤትን ነገ ይፋ እንደሚያደርግ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የዩኒቨርስቲ መግቢያና ወደ መሰናዶ ማለፊያ ነጥብን ለመወሰን  ፥ የዩኒቨርስቲዎችን ቀጣይ የመቀበል አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት መወሰኑንም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው። በአጠቃላይ 548 ሺህ 138 ተማሪዎች የ10 ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተናውን ወስደው 70 በመቶዎቹ 2 ነጥብ እና ካዛ በላይ ውጤት ሲያስመዘግቡ ፥ በተመሳሳይም የ12ኛ ክፍልን የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናን ከወሰዱት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ተፈታኞች ከ350 ነጥብ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን ቀደም ሲል  የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ኤጀንሲ አስታውሷል ። በነገው እለትም የሁለቱም ፈተናዎች የመቁረጫ ውጤት ይፋ ይደረጋል ተብሏል።