ሰሞኑን፣ ጥያቄውን ላለመመለስ ብቻ ተብሎ “ሲዳማ ክልልነቱን ካወጀ ክልሉ ይፈርሳል፤ ክልሉ እንዳይፈርስ ደግሞ የአገር መከላከያ ጦር እርምጃ መውሰድ አለበት፤” የሚሉ የተሳሳቱና (ሕዝብን) አሳሳች ወሬዎችን መንዛት ጀምረዋል–የመንግሥት ሰዎች። ይሄ ትክክል አይደለም።
1. ሲዳማ ክልልነትን መጠየቁ ሕገ-መንግሥታዊ መብት ነው። ክልልነትን መከልከሉ ሕገ-መንግሥቱን አለመታዘዝ (መጣስ እና ፀረ-ሕገመንግሥት መሆን) ነው። ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ውስጥ የሚከተው፣ ይሄን መብት የአለማክበር ተግባር ነው።
2. ሲዳማ ክልል በመሆኑ የደቡብ ክልል automatically ይፈርሳል የሚለው አባባልም ትክክል አይደለም። ሲዳማ ክልል በመሆኑ ብቻ ወዲያውኑ (automatically) የሚፈርስ ክልል የለም፣ አይኖርምም። ሲዳማ ክልል ሲሆን፣ ደቡብ ክልል፣ ሌሎቹን ዞኖቹን ይዞ ይቀጥላል። (ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ሲለይ ሱዳን አልፈረሰም። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትለይ ኢትዮጵያ አልፈረሰችም። ሲዳማ ከደቡብ ሲለይ ደቡብ ክልል ለምን ይፈርሳል–ለማፍረስ ሰበብ ካልፈለጋችሁ በቀር?!?)
3. የሲዳማን ጥያቄ ሕገ-መንግሥታዊ ምላሽ በመስጠት ለንትርኩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ፣ ወታደራዊ ኃይል በመመደብ ሲዳማ ላይ እንዲዘምት ጦሩን ማዘጋጀት መንግሥታዊ እብደት ነው። (ወይዘሮ ሙፍሪያት–በአብይ ትዕዛዝ–እያደረገች ነው ተብሎ እንደሚነገረው፣ ፊንፊኔ ላይ የደቡብን ልዩ ኃይል ኃላፊዎች ጠርታ በዝግ ስብሰባ ለጦርነት ማዘጋጀት፣ ወይም አብይና ጦረኛ አማካሪዎቹ እንደሚሉት የፌደራል ጦር ሰራዊትን ለማሰማራት መሞከር፣ ከመፍትሄ ይልቅ ችግር፣ ከሰላም ይልቅ የማያባራ ጦርነትን መጋበዝ ነው።)
በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ፣ የመከላከያ ሠራዊቱን የአገር ውስጥ የፖለቲካ መፍትሄ አካል አድርጎ መውሰድ ፍፁም ሕገ-መንግስታዊነትን መጣስ ወይም መቃወም ነው። ለሥርዓተ አልበኝነት በር የሚከፍተውም ይሄው ተግባር ነው።
ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን እና የአገር ዳር ድንበር የመጠበቅ ግዴታ ብቻ ያለውን የመከላከያ ሠራዊት፣ ለፖለቲካ አፈና መጠቀም ለሕወኅት መሪዎችም ያላዋጣ የአምባገነንነት መንገድ ነው።
4. ለሲዳማ ጥያቄ ተገቢውን ሕገ-መንግሥታዊ ምላሽ ወቅታዊነቱን ባገናዘበ መልኩ አለመመለስ፣ አሁን ላለንበት ፍጥጫ ዳርጎናል።
ሲዳማ፣ መብቱን ባግባቡ ሲጠይቅ፣ ዘመናትን ባስቆጠረ ሂደት ውስጥ፣ ወቅታዊነት ባለው መልኩ ባለማስተናገዳችን ምክንያት፣ የእራሱን ክልልነት ቢያውጅ፣ ‘ሌሎች ዞኖች በፉክክር ተነሳስተው (ወይም ሌሎች ነውጠኞች ከአራት ኪሎ ቤተመንግሥት ቀስቅሰዋቸው) እነሱም ክልልነትን ሊያውጁ ይችላሉ’ የሚል ማስፈራሪያም ይደመጣል። ሌሎች ብሔሮች ጥያቄ ካላቸው ልክ እንደ ሲዳማ ሕጋዊ መንገዱን ተከትለው ማቅረብ ይችላሉ፣ ይገባቸዋል። የሚመለከታቸው ሕገመንግሥታዊ ተቋማትም በሕግ አግባብ ሊያስተናግዷቸው ይገባል። የነሱን ጥያቄ በአለመመለስ ለሚፈጠር ችግር፣ ተጠያቂው፣ ተገቢ ምላሽ ያልሰጠው መንግሥት ነው እንጂ፣ መብቱን በሕጋዊ መንገድ ጠይቆ ያልተስተናገደውና የተገፋው የሲዳማ ሕዝብ አይደለም።
ሕገ-መንግሥታዊ ሂደቱን ያሟጠጠውን ሲዳማን እና አሁን ገና ብቅ ብቅ ያሉ ጥያቄዎችን በአንድ ዓይን በማየት በሁለቱ መካካል ተመሳሳይነትን መፍጠር (ወይም moral equivalence መመሥረት) ተገቢም ፍትሃዊም አይደለም።
5. አሁንም፣ (ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሊያደርግ ያስባል እንደሚባለው) የሲዳማን ጥያቄ በማፈን፣ በማናለብኝነት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ፣ በዘፈቀደ፣ እና ከላይ ወደታች በሆነ አሰራር፣ 4 ሌሎች የክልሉን ዞኖች ወደ ክልልነት ‘ለማሳደግ’ (በጥናት ሥም) ከመሯሯጥ ይልቅ፣ ቀኑ ሳያልቅ፣ ምርጫ ቦርድ፣ የማይቀረውን ሕዝበ-ውሳኔ ለሲዳማ ሕዝብ በማደራጀት ሕገ-መንግሥታዊና ታሪካዊ ግዴታውን ለመወጣት ቢሞክር ያዋጣዋል።
ምርጫ ቦርድ ይሄን ማድረግ ቢያቅተው ግን፣ የሲዳማ አስተዳደር ሬፈረንደምን የሚመለከት የውሳኔ ሃሳብ (Resolution) በምክር ቤቱ አሳልፎ፣ እራሱ ህዝበ-ውሳኔው የሚያካሄድበትን ሂደት መጀመር ይጠበቅበታል።
የሲዳማ አስተዳደር፣ ሕዝቡ ድምፁን የሚሰጥባቸውን ጣቢያዎችና ሁኔታዎች ለይቶና አመቻችቶ፣ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎች ታዛቢዎችን በመጋበዝ፣ ሕዝቡ በነፃነት ድምፁን በመስጠት እንዲወስን የማመቻቸት ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት። ሸክሙ ከባድ ቢሆንም፣ ይሄ ትውልድ ይሄንን ኃላፊነት ለመወጣት ብቃት እንዳለው በፍፁም አልጠራጠርም።
6. ይሄን እያደረጉ በተጓዳኝ፣ (ሊወለድ ያለው) የሲዳማ ክልልና የደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል፣ ሃዋሳ ከተማ ላይ ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት፣ በመወያየት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ መጀመር አለባቸው።
ሃዋሳ፣ የሲዳማ ከተማ መሆኗን ማንም ሊክድ አይችልም፣ አይገባምም።
የደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል፣ ሌላ ዋና ከተማ መርጦ፣ በከተማው ያሉትን ጽሕፈት ቤቶቹንና መስሪያ ቤቶቹን ወደ ሌላ የክልሉ ከተማ እስከሚያንቀሳቅስ ድረስ፣ በጊዜያዊነት (ጊዜውን በድርድር ማስረዘምም ማሳጠርም ይቻላል!) ሃዋሳን የመጠቀም ዕድል ቢሰጠው ሁኔታውን በተረጋጋ መንገድ ማስኬድ ይቻላል የሚል ዕምነት አለኝ።
በሕጋዊ መንገድ የቀረበን ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ በወታደራዊ መንገድ ለመመለስ መሞከር፣ ወይም መርሕ በሌለው ህሊና ቢስ የሃበሻ ሸፍጥ ታግዞ ግርግር በመፍጠር የሲዳማን መብት ለማድፋፋት መሞከር ጥፋትን መጋበዝ ነው። ይሄ ደግሞ የሕዝቦችንና የአገርን ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚከት ቀውስ ነው።
የሲዳማ ጥያቄ ቀላል ሕገ-መንግሥታዊ ምላሽ አለው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ይሄን ቀላል ምላሽ ያለውን ትልቅ ጥያቄ በመመለስ፣ የመጀመሪያውን ታሪካዊ ፈተናውን ማለፍ ይችላል። ወታደራዊ መፍትሄ በመፈለግ ይሄን ፈተና ከወደቀ ግን፣ ከዚህ በኋላ ሌላ ምንም ዓይነት ፈተና እንደማያልፍ፣ ለሥልጣኑም የመጨረሻው መጀመሪያ መድረሱን ያመላክታል።
Will he choose to pass the easier test of upholding justice by adhering to constitutionalism, or will he be just another Ethiopian thug, only with some narcissistic proclivities this time? Time will tell!
Comments
Post a Comment