የመንገድ ትራፊክ ደንብ የሚተላለፉ እግረኞችን የሚያስተምር ቅጣት ተግባራዊ ሊደረግ ነው – የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን

በተሻሻለው ደንብ ቁጥር 395/2009 መሰረትም በእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ላይ የተጣሉትን ቅጣቶች ለማስፈጸም የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን መመሪያ አዘጋጅቷል።
ደንቡ ለጥፋቶች እንደየክብደታቸው 40 ብር እና 80 ብር በቅጣት እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ሲሆን በደንቡ ከተጠቀሱት ጥፋቶች አንዱን ፈፅሞ ክፍያ መፈጸም ያልቻለ ወይም ያልፈለገ ማንኛውም ሰው ተመጣጣኝ የሆነ ማህበራዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል።
በባለስልጣኑ የመንገድ ደህንነት ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክተር አቶ ዮሃንስ ለማ ለኢዜአ እንዳሉት በትራፊክ አደጋ ከሚደርሱ ጉዳቶች ከፍተኛው ተጎጂም እግረኞች ናቸው።
ዳይሬክተሩ በአዲስ አበባ የትራፊክ አደጋዎች ካደረሱት ጉዳቶች 80 በመቶ ያህሉ በእግረኛ ላይ የደረሱ መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ደንቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው ሙከራ ያመጣው ውጤት ተገምግሞ ሙሉ በሙሉ የሚተገበር እንደሚሆንም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ታመነ በሌ በበኩላቸው ደንቡን ለመተግበር ካለፈው ዓመት ጀምሮ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በሁለት ወራት ውስጥ በቀለበት መንገዶች፣ ዋና ዋና መንገዶችና እግረኞች ያለአግባብ በሚያቋርጡባቸው ቦታዎች መተግበር የሙከራ ቅጣቱ እንደሚጀመር አብራርተዋል።
Comments
Post a Comment