አቶ ስምዖን ከበደ የማማከርና የሒሳብ ሥራ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ተማሪዎች ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ ‹‹የምርጫ ሥርዓትንና ሒደት በየትምህርት ቤታቸው መለማመድ አለባቸው›› የሚል ሐሳብ ይዘው ተግባራዊ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በአገር ደረጃ ለሚታቀደው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አሁን ከሚታዩ የተለያዩ የፖለቲካ አተያዮችና ሥነ ሥርዓቶች ባሻገር፣ በጉዳዩ ላይ ከታችኛው ደረጃ ጀምሮ ልጆች ላይ ቢሠራ የተሻለ ውጤት ሊያመጣ ይችላል የሚል ዕምነት አላቸው፡፡ ይህንንም ዕቅድ ወደ ተግባር ለመቀየር የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት ማነጋገር መጀመራቸውን ይገልጻሉ፡፡ በአጠቃላይ ምን ማድረግ እንዳቀዱና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ነአምን አሸናፊ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ተማሪዎች የምርጫ ሥርዓትና አሠራርን ከትምህርት ቤት ጀምረው ሊለማመዱትና ሊያዳብሩት ይገባል የሚል ሐሳብ ይዘው በመነሳት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ለትምህርት ሚኒስቴር አቅርበው እየሠሩ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ያነሳሳዎት ምክንያት ምንድነው?
አቶ ስምዖን፡- የዚህ ሐሳብ መነሻ የስድስት ዓመት ልጄ ነች፡፡ ወደፊት ምን መሆን ትፈልጊያለሽ? ብዬ ስጠይቃት፣ ‹‹ዶ/ር ዓብይን መሆን እፈልጋለሁ፤›› የሚል ምላሽ ሰጠችኝ፡፡ ምላሿ አስደነገጠኝ፡፡ መደንገጤንም ዓይታ፣ ‹‹ሴት መሆን አትችልም እንዴ?›› ብላ ጠየቀችኝ፡፡ ይቻላል የሚል ምላሽ ሰጥቻት፣ እንደ ዶ/ር ዓብይ ለመሆን ግን ብዙ መሥራትና ራስን ማዘጋጀት እንዳለባት አስረዳኋት፡፡ በዚህ ጥያቄ መሠረት ሌሎች ተማሪዎችም እንዴት ራሳቸውን መቅረፅ ይችላሉ? ራሳቸውን እንዴት ማዘጋጀት ይችላሉ? ብዬ በማሰብ የዚህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ለማዳበርና መሠረታዊ ነገር ሊያገኙ የሚችሉት በትምህርት ቤት በሚያደርጉትና በሚለማመዱት፣ የተማሪዎች ምርጫ ላይ ቢሳተፉ ነው ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ነው፡፡ ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው ውስጥ በሚያደርጉት ምርጫ በርካታ ነገሮች ሊማሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ በሚኖር የምረጡኝ ቅስቀሳና ሌሎች ከዚህ ሒደት ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ፣ በርካታ ክህሎቶችን ሊያዳብሩና ዴሞክራሲያዊ ምርጫንም ሊለማመዱ ይችላሉ ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደ አገር ለሚታሰበው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የራሱን ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ስለዚህ ልጄን እንዴት አድርጌ ነው ወደዚህ መስመር መክተት የምችለው? ጠያቂና ገለልተኛ ዜጋ አድርጌ መቅረፅ የምችለው? ብዬ ሳስብ ያገኘሁት ነገር ይህ ብቻ ነው፡፡ የሲቪክና የሥነ ምግባር ትምህርት እንደሚፈለገው ሊቀርፃቸው አልቻለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡበት ትምህርት ቢኖር ሲቪክና የሥነ ምግባር ትምህርት ነው፡፡ በሀልዮት ደረጃ፣ በተግባር ግን ምንም ዓይነት ለውጥ እያመጡ አይደለም፡፡ ስለዚህ ራሳቸው ተማሪዎቹ እንዲለማመዱት፣ እንዲረዱትና በተግባር እንዲሞክሩት ለማድረግ ያለመ ሐሳብ ነው፡፡ ዴሞክራሲ አንዴ ተሠርቷል ተብሎ የሚቆም ነገር አይደለም፡፡ በየጊዜው መታደስና እንክብካቤ ይሻል፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች ባህል መሆን አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ ዋነኛ ማስተማመኛው ደግሞ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ነው፡፡ ስለዚህ የእኔ ሐሳብ ተማሪዎች ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምረው ነፃና ፍትሐዊ ምርጫን መለማመድ እንዳለባቸው ከማሰብ የመነጨ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለምርጫ ስንነጋገርና በአገር አቀፍ ደረጃ ባህል እንዲሆን ሲሠራ በዋነኛነት የምርጫ ቦርድ ድጋፍና ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ከምርጫ ቦርድ ጋር ያለዎት ግንኙነት ምን ይመስላል? እነሱስ ሐሳብን እንዴት ተቀበሉት?
Comments
Post a Comment