የፖለቲካ ፓርቲዎች የስምና የመለያ ለውጦች ፋይዳና አንድምታ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት፣ በግንባሩ አባል ድርጅቶች የተደረጉ ጉባዔዎች አዳዲስ ክስተቶች የታዩባቸውና ባልተለመደ ሁኔታ አባል ድርጅቶች አዲስ ዓርማና መጠሪያዎችን ያስተዋወቁባቸው ናቸው፡፡
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ብሎ ስሙን የቀየረው የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) አስቀድሞ ስያሜውንና ዓርማውን እንደሚቀይር የታወቀ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ቀድሞ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በመባል ይታወቅ የነበረው የኢሕአዴግ አባል ፓርቲ ስያሜውን ወደ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) መቀየሩን ይፋ አድርጓል፡፡
ምንም እንኳን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሐዋሳ ባካሄደው ድርጅታዊ ጉባዔ አንዱ አጀንዳ የነበረው የፓርቲውን ስያሜ መቀየር ቢሆንም፣ ይህ የፓርቲውን ስያሜና ዓርማ የመቀየር አጀንዳ ውሳኔ ሳይሰጥበት ቀርቷል፡፡
ዓርማቸውንና ስያሜያቸውን የቀየሩት ኦዴፓና አዴፓ መሆናቸው በኢሕአዴግ ውስጥ የሚኖርን የኃይል አሠላለፍ የሚያሳይ እንደሆነ አስተያየታቸውን የሚሰጡ አሉ፡፡
ፓርቲዎች መጠሪያና መለያ ዓርማ (ብራንድ) ለምን ይቀይራሉ?
መለያ ወይም ብራንድ በንግዱ ዓለም በስፋት የሚታወቅ ጽንሰ ሐሳብ ሲሆን፣ ተቋማት ራሳቸውን ቀላልና ለመያዝ በማያስቸግር መንገድ እንዲታወቁ የሚረዳቸውን ምልክት በመጠቀም፣ በተጠቃሚዎቻቸው ዘንድ ለመታወቅ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም ለተጠቃሚዎች የእነዚህን ድርጅቶች ምርቶችና አገልግሎቶችን በዓርማቸው የመለየትና የመምረጥ ዕድል የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ረዘም ላለ ጊዜ ሲቆይና በሰፊው ሲታወቅ ተዓማኒነትንም ይዞ ይመጣል፡፡ እነዚህ መለያዎች የድርጅቱ መጠሪያና መለያ ምልክትን የሚያካትቱ ሆነውም ይስተዋላሉ፡፡
ልክ እንደ ንግድ ድርጅቶች ፓርቲዎችም መለያዎችን (ብራንድ) በመያዝ የሚታወቁ ሲሆን፣ ፓርቲዎች ምልክቶቻቸውን፣ የያዙትን ዓላማ፣ የሚከተሉትን ርዕዮተ ዓለምና የወፊት ራዕያቸውን በሚያመላክት መንገድ ይቀርፃሉ፡፡ በእነዚህ መለያዎቻቸው ለመራጮቻቸው የፓርቲያቸውን ዕጩዎች የሚያስተዋውቁ ሲሆን፣ የርዕዮተ ዓለም ምልከታዎቻቸውንም ለመራጮቻቸው ያስተላልፉባቸዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠቀሙባቸውን ምልክቶች መቀየራቸውም በዓለም የተለመደ ክስተት ሲሆን፣ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ግን የፓርቲዎች ዓርማ መቀየር የተለያዩ ተፅዕኖዎች ይኖሯቸዋል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡
ሚ ሶን ኪምና ፍሬዴሪክ ሶልት የተባሉ የፖለቲካ ተመራማሪዎች ፓርቲዎች ለምን ስምና ምልክታቸውን እንደሚቀይሩ፣ ከሚሸከሟቸው የመረጃ እሴቶች አኳያ ለረዥም ጊዜ የቆየ መለያ የተሻለ ያገለግላል በሚለው እሳቤ መሠረት የፓርቲዎች መለያዎች የመቀየር ዕድላቸው አናሳ እንደሆነ ቢጠቅሱም፣ ይህ ሲሆን ደግሞ በፓርቲ ውስጥ በሚፈጠር ፈተና በጊዜው ያለውን ሁኔታ ለማስቀጠል የማይቻልበት ችግር ሲገጥም የሚደረግ እንደሆነ የሚታሰብ ነው ይላሉ፡፡ ይህም ያልተረጋጋና ደካማ የፓርቲ ተቋማዊ ሥርዓት አለመኖሩን ያመለክታል ይላሉ፡፡
ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው የሚቆሙት የቢዝነስና የፐብሊክ ፖሊሲ እንዲሁም የብራንዲንግ ባለሙያው አቶ እሸቱ ዱብ፣ የቢዝነስና የፖለቲካ ማርኬቲንግ የሚዋዋሱት ጉዳይ እንዳለ ጠቅሰው ፖለቲካ ውስጥ ገበያ እንዳለ ያሰምራሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በገበያው ውስጥ የማሸነፍ ዕድላቸው ከብራንድ ጋር ተያያዥ ስለሆነ ትልቅ ዋጋ ያለው እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
‹‹ብራንዲንግ ልብና አዕምሮን የማሸነፍ ጉዳይ ነው፣ ራስንም ለአጠቃላይ ወቅቱ በሚጠይቀው ቦታ ላይ ማስቀመጥ ነው፤›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡
ስለዚህ በዚህ ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ለ27 ዓመታት ይቅርና ለአምስት ዓመት የሚሠራም ስትራቴጂ ረዥም የሚባል ስለሆነ፣ ከጊዜው እኩል ለመራመድ ፓርቲዎች ራሳቸውን ማዘጋጀት ያስፈልጋቸዋል ይላሉ፡፡ ይህም ከሚሠራባቸው አንደኛው ጉዳይ የመለያ ምልክት ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ይኼንን ሲያብራሩም፣ በዴሞክራሲ ፓርቲዎች ሰዎችን ያስቀድማሉ፡፡ ስለዚህም ካለው የሕዝብ ፍላጎት ጋር ራስን አጣጥሞ መሄድ ስለሚያስፈልግ፣ እንዲህ ዓይነት የመለያ ለውጦችን ማድረግ ለፖለቲካ ፓርቲዎች አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡
ይሁንና ሚ ሶን ኪምና ፍሬዴሪክ ሶልት የፓርቲዎች የምርጫ ውድቀት ከመለያ ለውጦች ጋርም ግንኙነት እንዳለው ያሳያሉ፡፡ ፓርቲዎች ልክ የንግድ ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸው እንዲሸጥ እንደሚፎካከሩ ሁሉ፣ ፓርቲዎችም በተመሳሳይ ፉክክር ውስጥ ስለሚኖሩ የፓርቲ መለያዎች፣ የፖለቲካ መለያዎች፣ የርዕዮተ ዓለም መለያዎችና የመለያ መሪዎች ወይንም ‹ብራንድ ሊደርስ› የሚባሉት ቃላት በፓርቲ ጥናቶች ውስጥ በስፋት እየተስተዋሉ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

No comments