በከተማዋ ብሔር ተኮር መጠራጠር እንዲሰፍን በበሮች ላይ ቀለም በመቀባት የተሰራው ስራ በህብረተሰቡ እና በመንግስት ንቃት መክሸፉን የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ስኳሬ ሹዳ ገለፁ፡፡

Image may contain: 1 personምክትል ከንቲባው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከፊታችን ባለው መስከረም 17 ለሚከበረው የመስቀል ባዓል ለመላው የእምነቱ ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕከት አስተላልፈዋል፡፡

ከመስከረም 18 እስከ 21 በሀዋሳ ከተማ ለሚካሄደው የደኢህዴን 9ኛ ጉባኤ እንዲሁም ከመስከረም 23 እስከ 25 ‹‹በልማታዊ ዴሞክራሲ ማዕቀፍ የለውጥ እንቅስቃሴያችንን በማስቀጠል የኢትዮጵያን ህዳሴ እናረጋግጥ›› በሚል መሪ ቃል በከተማዋ ለሚካሄደው የኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤ ለመላው የድርጅቶቹ አባላትና ደጋፊዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል፡፡

በከተማችን ባለፉት 3 ቀናት በተለያየ አካባቢ በተለይም በታቦር፣ በምስራቅና በመናህሪያ ክፍለ ከተማ የተለያዩ ቀለሞችን በመኖሪያ ቤት በሮች ላይ በመቀባትና ቀለሙን ተከትሎ የብሔር ግጭት ሊኖር እንደሚችል በማስመሰል በተነዛ ወሬ የከተማዋ ህዝብ መጠነኛ ጭንቀት ውስጥ እንደገባ ይታወቃል፡፡


ይህን አስመልክቶ የከተማ አስተዳደሩ ከክልሉና ከፌደራል የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ሰፊ የፀጥታ ጥበቃና የጥናት ስራ ሲሰራ መቆየቱን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ስኳሬ ሹዳ ገልፀዋል፡፡


በዚህም መሰረት በከተማው በግለሰቦች መኖሪያ ግቢ በሮች ላይ የተቀባ ቀለም መኖሩን ማረጋገጥ እንደተቻለም አቶ ስኳሬ ገልጸዋል፡፡


እነዚህ ቀለሞች አንደኛው የከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት የቤቶች ደረጃ ምዝገባ ስራ ክፍል የቀባው ሲሆን ሁለተኛው በከተማዋ በቆሻሻ ማንሳት ስራ የተሰማሩ ማህበራት ገንዘብ የከፈሏቸውን ነዋሪዎች ካልከፈሉት ለመለየት የቀቡት መሆኑን ለመለየት እንደተቻለ ምክትል ከንቲባው ገልፀዋል፡፡


ከዛ ውጪ የተለየ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች ህዝቡን ለማሸበርና የከተማዋን ገፅታ ለማጉደፍ እንዲሁም በህዝቦች መካከል መተማመንና አብሮነት እንዳይኖር በማድረግ ብሔር ተኮር ጥርጣሬ ለማሳደር የቀቡት ቀለም መኖሩንም ለማረጋገጥ ተችሏልም ብለዋል፡፡


በሀገር ደረጃ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳይቀጥል ለማድረግና እንዲቀለበስ ፍላጎት ያላቸው ሀይሎች በተለያየ ጊዜና ቦታ ሲያደርጉት ከነበረው እንቅስቃሴ አንዱ እንደሆነም ለመረዳት እንደተቻለ አቶ ስኳሬ ገልፀዋል፡፡


በመሆኑም በተደረገው ክትትል ወቅት እኩይ ተግባር ማስፈፀሚያ የሆኑና ገንዘብ የሚከፈላቸው በልመና መስክ የተሰማሩ ጥቂት ግለሰቦች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉበት ሁኔታ መኖሩን የገለፁት ምክትል ከንቲባው ከእነርሱ ውጭ ከሌላ አካባቢ በመምጣት አልጋ በመከራየት ስለት ነገሮችን ይዘው ሲንቀሳቀሱ የተያዙ ፀጉረ ልውጦች መኖራቸውንም በመጠቆም ነው፡፡


ቀለም በበራቸው የተቀባባቸው ነዋሪዎችም ያለምንም ልዩነት አልፎ አልፎ የተቀባባቸው መሆኑም ተረጋግጧል፡፡ በዚህም በከተማው የሚኖሩ የደቡብ ብሔረሰቦች ላይ ብቻ ሳይሆን በከተማዋ በሚገኙ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በር ላይም መቀባቱ ተረጋግጧልም ብለዋል ምክትል ከንቲባው፡፡


እነዚህ አካላት ላይ በመደረግ ላይ ያለው ምርመራ ውጤቱ ለህዝብ ይፋ የሚደረግ ነው ያሉት አቶ ስኳሬ በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ሀይሉና ህብረተሰቡ በአንድ ላይ በመሆን አከባቢውን በንቃት እየጠበቀ መሆኑን ተከትሎ በከተማዋ ከተራ ሽብር እና ወሬ በስተቀር የተከሰተ አንዳችም ችግር አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡


በመሆኑም ከፊታችን ያለው የመስቀል በዓልም ይሁን በጉጉት የሚጠበቀው የደኢህዴንና የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤን በከተማዋ ለማክበር ምንም አይነት የፀጥታ ችግር እንደማይገጥም ገልጸው የከተማው ነዋሪዎችና ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች ስጋት እነዳይገባቸው አሳስበዋል፡፡

ውበት ለከተማችን፤ ስኬት ለህዝባችን…!


ምንጭ፤ ሀዋሳ መ.ኮሙ

No comments