በሀዋሳ ሀይቅ ላይ የተጋረጡ ችግሮች የሀይቁን ህልውናና የብዝሃ ህይወት ሀብት አደጋ ላይ የሚጥሉ መሆናቸውን በሀይቁ ዙሪያ የተደራጁ ወጣቶች ገለፁ።
በሀይቁ ዙሪያ በተለያዩ ስራዎች ተደራጅተው የሚሰሩ ወጣቶች ምንም እንኳን የየራሳቸው ሳምንታዊ የፅዳትና እንክብካቤ መረሃ ግብር አውጥተው ሀይቁን ለመታደግ እየሰሩ ቢሆንም ከሀዋሳ ከተማ በለይም ከግዙፍ የመንግስት ተቋማትና ፋብሪካዎች የሚለቀቁ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች ሳይታከሙ በቀጥታ ወደ ሀይቁ የሚገቡ በመሆናቸው ጥረታቸውን ውጤት አልባ እያደረገባቸው እንደሆነ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ከሀዋሳ ከተማ የሚወገድ ፍሳሽ ቆሻሻ እና በሀይቁ ዙሪያ ካሉ የእርሻ ማሳዎች የሚገባ ደለል ሀይቁ እንዲሞላና የውሃ መጠኑም እንዲቀንስ በማድረግ የሀይቁ ወቅታዊ ፈተናዎች ሆነዋል።
ለመስኖ እርሻ እና ለከተማ አረንጓዴ ስፍራዎች መጠኑ ከፍ ያለ ውሃ በየቀኑ በቦቲ መኪና ከሀይቁ የሚቀዳ መሆኑ እንዲሁም በህገ ወጥ አሳ አስጋሪዎች አማካይነት በበቂ ሁኔታ ያልጎለመሱ ዓሳዎች በየእለቱ የመረብ ሲሳይ መሆናቸው የሃዋሳ ሀይቅን የብዝሃ ህይወት ሀብት ስጋት ውስጥ ጥሎታል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲው መምህር ሶሬሳ በላይ፥ ባሁኑ ወቅት በሀዋሳ ሀይቅ የውሃ ላይ የሚታየው ሳር ከቅርብ አመታት በኋላ እየተስፋፋ የመጣ መሆኑን በመጥቀስ ምልክትነቱን ከሀይቁ አደጋ ጋር ያያይዙታል።
በ1998 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲያቸው ‘’የሃዋሳ ሀይቅ አያያዝ አሁን ባለበት ከቀጠለ ከ50 አመታት በኋላ የመንጠፍ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል’’ የሚል ጥናት ማካሄዱንም ያስታውሳሉ።
በዚህም የሀዋሳ ሀይቅ ዛሬም (ከ13 አመታት በኋላ) መሰል የህልውና አደጋ ላይ በመሆኑ ሀይቁንና ሁለገብ አገልግሎቱን ለማዳን የቀሩት 37 አመታት ብቻ መሆናቸውን በማንሳት የተሻለ ትኩረት እና ጥበቃ ሊያገኝ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የሃዋሳ ከተማ አካባቢ ጥበቃ እና ደን ፅህፈት ቤት የተጠቀሱት ችግሮች መኖራቸውን ባካሄደው ጥናት ማረጋገጡን በመግለፅ፤ የተለያዩ የጥበቃ ስራዎች መከናወን መጀመራቸውን አስታውቋል።
ከነዚህ መካከል በሀይቁ 5 ዋና ዋና መግቢያ በሮች የሚገባውን ደለል ለመከላከል የእርከን አጥር(ጋቢዮን) እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።
በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ ግዙፍ የመንግስት ተቋማት፣ ፋብሪካዎችና ሆቴሎች ለሀይቁ መበከል መንስዔ በመሆናቸው አዲስ የመቆጣጠሪያ ህግ ወጥቶላቸው ተግባራዊ መሆን እንደጀመረም ፅህፈት ቤቱ ጠቁሟል።
Comments
Post a Comment