
የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት አቶ ቃሬ ጫዊቻ በዞኑ በየአከባቢው የረጅም ጊዜ የህዝብ ጥያቄና የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው የቆዩ ጉዳዮችን የህዝብን ፍላጐት መሠረት ባደረገ መልኩ ለመፍታት እንደሚሠሩ በሰጡት መግለጫ ገልፀዋል፡፡
በሀገራችን የተፈጠረው የለውጥ ሂደት የሲዳማ ህዝብም የሚጋራው በመሆኑ ይህንን ለውጥ ማስቀጠልና የህዝባችንን ፍላጐት ማርካት የመጀመሪያውና ዋናው ተልዕኳቸው መሆኑን ጠቁመው የሲዳማ ህዝብ ለሠላም፣ለልማት፣ለእድገት ቅድሚያ የሚሰጥና ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር ተፋቅሮና ተከባብሮ የመኖር ባህሉን በተግባር ያሳዬ፤እንግዳ ተቀብሎ ዘመድ የማድረግ ተምሳሌትነቱ ለሌላውም የሚተርፍ እሴት ያለው ህዝብ መሆኑን አመልክተው ህዝቡ ልዩነት የሚያጐሉ፣የሀገሪቱን እድገት የሚያጓትቱ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ወደ ጐን በመተው ከአጐራባች ክልሎችና ዞኖች ጋር እንዲሁም በውስጡ ከሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በፍቅርና በሰላም አብሮ የመኖር እሴት ለረጅም ዘመናት ያጐለበተ ህዝብ መሆኑን በመጠቆም ይህንን አኩሪ ባህሉን በመጠቀም ለአከባቢው ሰላምና ለሀገራችን አንድነት የበኩሉን ሚና መጫወት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የሲዳማ ህዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ሆኖ የቆየው ክልል ሆኖ የመደራጀት ፍላጐት ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደዉ መሠረት በቅርቡ በዞኑ ምክር ቤት ፀድቆ ለክልሉ ምክር ቤት መቅረቡን አስታውሰው ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ የዞኑ አስተዳደር ጉዳዩን በባለቤትነት እንደሚከታተልና አስፈላጊና ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝቡ የመስጠት ስራን በኃላፊነት እንደሚወጣ ዋና አስተዳዳሪው በመግለጫቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የህዝብን ፍላጐት መሠረት ባደረገ መልኩ ኅብረተሰቡ በቅርበት መልካም አስተዳደርና ፍትህ እንዲያገኝ ታሳቢ በማድረግ የዞንና የወረዳ መዋቅሮች እንዲጠኑ የክልሉ መንግስት ቀደም ብሎ በወሰነው ውሳኔ መሠረት በዞኑ በተለያዩ አከባቢዎች እየተደረገ ያለውን ጥናት ተከትሎ የወረዳ መዋቅር ጥናት የተጀመረው የክልል ጥያቄን ለማኮላሸት ነው ተብሎ የሚሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን ጠቁመው የክልል ጥያቄው አሁን እየተሰራ ካለው ወረዳ መዋቅር ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ገልፀው ጥያቄው በህገ-መንግስቱ መሠረት የሚፈታና ምላሽ የሚያገኝ ጉዳይ መሆኑን ጨምረው ጠቁመዋል፡፡
የወረዳ መዋቅር ጥናት የራሱ መመዘኛና መስፈርት ያለውና በሌሎች ዞኖችም ቀደም ተብሎ የተጀመረ ተግባር መሆኑን ገልፀው አሁን በዞኑ ጥናት በተጀመረባቸው ቦታዎች እዚም እዛም "ወረዳ ይገባናል" በሚል የሚነሱ ጥያቄዎች መኖራቸውን በመጥቀስ ለአደረጃጀት የተቀመጠውን መመዘኛ ማዕከል ባደረገ መልኩ ብቻ የሚፈፀም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የህዝቡ የለውጥ ፍላጐት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው ህዝባችንን በኢኮኖሚ፤በማህበራዊና በፖለቲካው መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በሀገራችን የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል በሚሠራው ሥራ ላይ የዞኑ አስተዳደር ከብሔሩ ምሁራንና ወጣቶች ጋር ተቀናጅቶ በቅርበት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡
ሌላው መስተካከል ያለበትና በአጭር ጊዜ ውስጥ መታረም የሚገባው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አከባቢ ያለው አላስፈላጊ ብሮክራሲ ማብዛትና ህብረተሰቡን በቀጠሮ የማመላለስ ሁኔታ ህዝቡን የሚያበሳጭና በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርግ በመሆኑ በየደረጃ ካለው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ህብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ የማድረግ ስራ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በዞኑ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን፣የመሠረተ ልማት ፍላጐቶችንና አሁን በሀገራችን እየታየ ያለውን የለውጥ ሂደት ለማስቀጠል ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ መስራትና ለውጡን ማስቀጠል እንደሚገባ አስምረው አሁን በደረሱ በተለይ የመኸርና የትምህርት ተግባራት ላይ መረባረብ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ነሐሴ 3/2010
ሀ ዋ ሳ
ምንጭ
Comments
Post a Comment