Skip to main content

የዲሞክራሲያዊ ልማት ውርስበሰለሞን ጎሹ
አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በራሳቸው ልዩ ባህሪያትና እንቅስቃሴዎች ላይ ተመሥርቶ ከመፈረጅ ይልቅ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ማነፃፀር እየተዘወተረ ነው፡፡
ለዚህ አንዱ ምክንያት ራሳቸው ኃይለ ማርያም መለስን ከአንደበታቸው አለማራቃቸው ነው፡፡ በኢኮኖሚ ዕውቀታቸው ዓለም አቀፍ አድናቆት የተቸራቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ትንታኔ የመስጠት ልማድ የነበራቸው ሲሆን፣ ለፓርላማ በሰጡት ማብራሪያና ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ዝርዝር የኢኮኖሚ ትንታኔ ውስጥ ከመግባት ይልቅ አንኳር ጉዳዮች ላይ ብቻ ማተኮር መርጠዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አካሄድ የኢትዮጵያን ልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ከዲሞክራሲ ጋር ካለው ግንኙነት አንፃር የሚነሱትን የተለያዩ ጥያቄዎች እንዴት አድርጎ ያስተናግዳል የሚል ጥያቄም መነሳቱ አልቀረም፡፡

ዲሞክራሲያዊ ልማት

ኢትዮጵያ የልማታዊ መንግሥት ጽንሰ ሐሳብን ከምሥራቅ እስያ አገሮች ከመገልበጥ ይልቅ በሒደት ልታረጋግጠው የተነሳችበትን ዲሞክራሲ በመጨመር ‘ዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት’ ለመመሥረት መወሰኗ በይፋ የተገለጸው የሚሊኒየምን በዓል ባከበረችበት የ2000 ዓ.ም. መባቻ ላይ ነበር፡፡

ልማታዊ መንግሥታት በመንግሥት ጣልቃ ገብነት፣ ሰፊ ቁጥጥርና ዕቅዶች እየታገዙ የሚጓዙ ሲሆን ነፃ ገበያ፣ ብሔራዊ ስሜት፣ የውጭ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ሰፊ የመንግሥት ቢሮክራሲ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሕዝብ ተቀባይነት፣ ከልሂቃን ጋር አብሮ የመሥራት ባህል፣ ከግል ዘርፉ ጋር ተባብሮ ማደግ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ፣ የሕግ የበላይነት፣ የሚዲያና የሲቪል ማኅበራት ተሳትፎና የሙያና የብዙኅን ማኅበራት እንቅስቃሴ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች አስማምቶ የሚያስቀጥል ጠንካራ አመራር ደግሞ የነገሮች ሁሉ መቋጫ ነው፡፡ ውጤታማና አስተማማኝ ልማታዊ መንግሥት ሌላው መለያው የመሠረተ ልማት ግንባታ ነው፡፡

ይሁንና ከ1960ዎቹ ጀምሮ የሚታወቀው የልማታዊ መንግሥት ጽንሰ ሐሳብ በፀረ ዲሞክራሲያዊነቱና ለሙስናና ለኪራይ ሰብሳቢነት መስፋፋት ካለው አስተዋጽኦ ጋር ተያይዞም አብሮ ስሙ ይነሳል፡፡ ልማታዊ መንግሥታት ሁሉ ፀረ ዲሞክራሲ ሊሆኑ እንደማይችሉ፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትም ከልማታዊ መንግሥታት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት እንደሌላቸው ሟቹ አቶ መለስ በቃልም ይሁን በጽሑፍ፣ በፖለቲካ መድረኮችም ይሁን በአካዳሚክ መጽሐፎች ላይ ወይም ኮንፈረንሶች ላይ በመገኘት ይሟገቱ ነበር፡፡ በርዕዮተ ዓለም ደረጃ ዋነኛው ግብ የተቀባይነት ምንጭ የተፋጠነ ልማት እንደሆነ የሚገልጹት አቶ መለስ፣ በቅርፅ ደረጃ ኢትዮጵያ ለዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት የተመቸ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የተለያዩ ተቋማትና ነፃ መንግሥት እንዳላት ይከራከሩ ነበር፡፡

ኢሕአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ (ግንባር) በአብዮታዊ ዲሞክራሲም ሆነ በዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለሙ ለዲሞክራሲ መረጋገጥ ሁሌም ቦታ ይሰጣል፡፡ ፓርቲው አብዮታዊ ዲሞክራሲን ትቶ ነው ወይስ በተጨማሪነት ዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥትን የያዘው የሚለው ክርክር እንዳለ ሆኖ፣ ቢያንስ በዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት ጽንሰ ሐሳብ ይበልጥ ለዲሞክራሲ ቦታ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑ ከ2000 ዓ.ም. በኋላ የተጠበቀ ቢሆንም፣ በቀጣዮቹ ዓመታት በሕግ ማውጣት፣ በፍትሐ አስተዳደርና ከሌሎች የሙያና የብዙኅን ማኅበራት ጋር ፓርቲው የነበረው ግንኙነት ዲሞክራሲን ወደ ኋላ የጎተተ መሆኑን በመጥቀስ የሚተቹት አሉ፡፡

ልማታዊ መንግሥት ዲሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም በማለት የሚሞግቱ አካላት ኢሕአዴግ በልማት ስም ጥቂት ኃይሎችን ብቻ ተጠቃሚ በማድረግ አብዛኛውን ዜጋ ግን ከድኅነት ሊያላቅቅ የማይችል ርዕዮተ ዓለም በመከተል፣ የወሳኝ የአማራጭ የፖለቲካ ኃይላትን ተሳትፎ ገድቦት መቆየቱን ይጠቁማሉ፡፡

አቶ አብርሃም ከበደ የኢኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ኢሕአዴግ ዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት ለመገንባት ያለው ዕቅድ የሚበረታታ ቢሆንም ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ የተጓዘበት መንገድ ብዙ እንደሚቀረው ይገልጻሉ፡፡ ‹‹አቶ መለስ ምንጊዜም የሚያፈልቁት ሐሳብ ከተለያዩ አገሮች ተጨባጭ እውነታ ቢቀዳም፣ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ከተለመዱ አማራጮች ወጣ በማለት ሦስተኛ የራሳቸውን አማራጭ ይፈጥራሉ፡፡ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሁለት የተለያዩ ዓለሞችን አቀላቅለዋል፡፡ በዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥትም እንዲሁ ሁለት የተለያዩ ነገሮችን ለማጣመር ሞክረዋል፡፡ ሁሌም ግን ግራ ዘመም አመለካከታቸው በተግባር ላይ ሲታይ ያመዝናል፤›› ይላሉ፡፡

አቶ አብርሃም በቅርቡ የወጣው የዓለም ባንክ ሪፖርት ማኅበራዊ ፍትሕ በማስፈን ኢትዮጵያ ለውጥ ማምጣቷን ቢጠቁምም፣ በተቃራኒ የአይኤምኤፍ ሪፖርት አብዛኛው ሕዝብ እየተጎዳ በመሆኑ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገቱን እንድታቀዛቅዝ መጠቆሙ ከዲሞክራሲ ጋር ግንኙነት እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በዲሞክራሲ ልማት፣ በልማትም ዲሞክራሲ ይመጣል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች በተለያዩ ምክንያቶች ብዙኅነት አለ፡፡ ንቃተ ህሊናው እየጨመረ በመጣ ቁጥር ሕዝቡ ዲሞክራሲያዊ ባህል እየተላበሰ ይመጣል፡፡ ሕዝቡ ኢሕአዴግን እየደገፈ የሚቀጥለው በሐሳቡ ሳይሆን በውጤቱ ነው፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት ማኅበራዊ ፍትሕ ከሌለና አብዛኛው ሕዝብ በድህነት እስካለ ድረስ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መንግሥትን አይመርጥም፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

ገበሬው ከኢሕአዴግ በሚያገኛቸው አንዳንድ ጥቅማ ጥቅሞች ምክንያት ተቃውሞውን ባያሰማም፣ የሠራተኛ ማኅበሩና ሌሎች የብዙኅን ማኅበራት ነፃነቱ ቢሰጣቸው ተቃውሞ የማሰማት ዕድላቸው ሰፊ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡ በአቶ መለስ መሪነት የተቀረፁት የኢኮኖሚ ሕጎችና ፖሊሲዎች በወረቀት ደረጃ ለዕርዳታ ሰጪ ተቋማትና አገሮች አማላይ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ሰነዶቹ ያቋቋሙዋቸው ተቋማት በወረቀት ላይ ነፃና ዲሞክራሲያዊነታቸው የተረጋገጠ በመሆኑ አንድ ዕርምጃ ቢሆንም፣ ጠንካራ ከሆኑ ጫና ይፈጥርብኛል ያላቸውን እንደ ፍርድ ቤቶች ያሉ ወሳኝ ተቋማትን መንግሥት ማዳከሙን ግን አቶ አብርሃም ይተቻሉ፡፡

በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ቢሮ የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ቻርልስ አቡግሬ ከአቶ አብርሃም የተለየ አቋም ነው ያለቸው፡፡ በዚህ ወር የ’ኒው አፍሪካን’ መጽሔት ላይ ‹‹Who was the real Meles Zenawi?›› በሚል ርዕስ በጻፉት ጽሑፍ፣ ‹‹አብዛኛው ሰው ከሚያምነው በተቃራኒ መለስ ከልቡ በዲሞክራሲና በሰብዓዊ መብት መከበር ያምን ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ቻርልስ አቡግሬ አቶ መለስ ዲሞክራሲና ልማታዊ መንግሥት አብረው ይሄዳሉ ብለው ያምኑ እንደነበርም መስክረዋል፡፡ ‹‹ዲሞክራሲም ሆነ ልማት በራሳቸው ብቻቸውን መሄድ እንደማይችሉ ያላቸውን እምነት እጋራለሁ፡፡ ሁለቱም እርስ በርስ የሚደጋገፉ ናቸው፡፡ የልማት ሒደቱ ዲሞክራሲያዊነት የሚረጋገጠው የብዙኅኑን ተሳትፎ ሲያረጋግጥ፣ ተለዋዋጭና ፍትሐዊ ሲሆን ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሒደቱ ልማታዊ የሚሆነው ደግሞ የተገለሉ አካላት የኢኮኖሚና የማኅበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ በመሆን በንቃት ፖለቲካውን ቅርፅ የማስያዝ ሚና ሲጫወቱ ነው፡፡ መለስ ይህን ‘ዲሞክራሲያዊ ልማት’ ይሉት ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ጸሐፊው ሌላው የሚያነሱት ነጥብ አቶ መለስ በፓርቲያቸው በኢሕአዴግ ልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለምን ወደ ኅብረተሰቡ በትምህርት፣ በፖሊሲና በአደረጃጀት ለማድረስ ባለው ቁርጠኝነት ይተማመኑ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ ከአቶ መለስ ጋር በሥራ አጋጣሚ ቅርርብ የነበራቸው ቻርልስ አቶ መለስ እሴት የማይጨምሩ የኪራይ ሰብሳቢነት እንቅስቃሴዎችን ለማስወገድ ጠንክረው ይሠሩ እንደነበር መስክረዋል፡፡ አቶ መለስ ፓርቲያቸው ራሱን ለማጠናከር የመንግሥትን ሀብት ይጠቀማል በሚል የሚቀርብባቸውን ክስ ከማስተባበል ይልቅ አስፈላጊ መሆኑን ብቻ ይከራከሩ እንደነበር ቻርልስ ያስገነዝባሉ፡፡

የአቶ መለስ የዲሞክራሲያዊ ልማት ጽንሰ ሐሳብ በአፍሪካ ባሉ አገሮች ሊተገበር እንደሚገባ የሚመክሩት ቻርልስ አመፅን ለመቆጣጠር ቢሆንም እንኳን ሰዎች ላይ መተኮስ፣ በርካታ ጋዜጠኞችን ማሰርና የመሳሰሉ ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ግን ከአቶ መለስ ጋር እንደሚያለያዩዋቸው ይጠቁማሉ፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ ዶ/ር መድኅኔ ታደሰ ‹‹Meles Zenawi and the Ethiopian State›› በተሰኘ የቅርብ ጊዜ ጽሑፋቸው፣ አቶ መለስ ኢትዮጵያን ልማታዊ መንግሥት ለማድረግ በርካታ ሌሎች ጉዳዮችን መጨፍለቃቸውን ያስረዳሉ፡፡ አቶ መለስ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የዋለ ኢንቨስትመንት፣ ፖለቲካዊ ቁጥጥር፣ ገበሬውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የሀብት ቁጥጥር ላይ ትኩረት ያደርጉ እንደነበር የሚገልጹት ዶ/ር መድኅኔ፣ ለኢኮኖሚው ሽግግር ሰላምና መረጋጋት፣ ብሔር ተኮር አደረጃጀት፣ ማኅበራዊ ዝውውር፣ ጠንካራ መንግሥት፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውርን እንደ ቅድመ ሁኔታ ይወስዱ እንደነበርም ይገልጻሉ፡፡ አቶ መለስ ሁሉንም ቅድመ ሁኔታዎች መፍጠራቸውን ዶ/ር መድኅኔ ያስገነዝባሉ፡፡

አቶ መለስ የልማታዊ መንግሥት መሠረት እንዲይዝ ለማድረግ ሲሉ የዲሞክራሲ ሒደቱን ማዘግየታቸውን አልያም ጨርሰው መርሳታቸውን ዶ/ር መድኅኔ ይገልጻሉ፡፡ ሰብዓዊ መብት፣ ነፃ ፕሬስ፣ ጠንካራ ፓርላማ፣ በጨቅላ ዕድሜ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ልማታዊ መንግሥት አጀንዳ ያጨናግፋል የሚል እምነት አቶ መለስ እንደነበራቸው ይተነትናሉ፡፡

አቶ እንዳልካቸው ገረመው የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት ሲሆኑ፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕገ መንግሥት መምህር ናቸው፡፡ አቶ እንዳልካቸው ከ1997 ዓ.ም. በኋላ ኢሕአዴግ በቁጥጥር፣ በተሳትፎ፣ በሕግ ማውጣት ሒደቱና በተቋማት ግንባታ ዙርያ ልማታዊ መንግሥትን ለማረጋገጥ ሕግን እንደ መሣርያ መጠቀሙን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ይህ የማሻሻያ ፕሮጀክት አሁን ተጠናቋል፡፡ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትና የቁጥጥር አድማስ በሕጋዊ መልኩ አሁን በጣም ጨምሯል፡፡ አሁን ያለው ሒደት ጥቂቶችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግና የሲቪልና የፖለቲካ መብቶችን ዝቅተኛ ቦታ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ለልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም የተመቸ አለመሆኑን አቶ እንዳልክ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች 51 እና 55 በምዕራፍ 2 ላይ ካሉት መሠረታዊ መርሆዎችና እሴቶች እንዲሁም በምዕራፍ 3 ላይ ካሉት መሠረታዊ መብቶች፣ ነፃነቶችና ከፖሊሲ መርሆዎች አንፃር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ ልማታዊ መንግሥት መተግበር ካለበት የተወሰኑት የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ለጊዜው መታገድ አለባቸው፤›› ይላሉ፡፡

ፋንቱ ፋሪስ የዓለም አቀፍ ንግድና ዓለም አቀፍ የልማት ፖሊሲ ኤክስፐርት ስትሆን በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህርት ነች፡፡ ልማታዊ መንግሥትን ለመመሥረት ከሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላትና መጓደል አንፃር አንድ ልማታዊ መንግሥት ዲሞክራሲያዊ ነው አይደለም የሚለው ነጥብ በጣም አከራካሪ መሆኑን ትጠቁማለች፡፡ ፋንቱ በተለይ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና በሕግ የበላይነት ላይ የአብዛኛው ዜጋ ስምምነት፣ ከተፅዕኖ ነፃ የሆነ መንግሥት ምሥረታ፣ የልሂቃኑና የመንግሥት ግንኙነት፣ የሲቪል ማኅበረሰቡና የሚዲያው ሚና፣ እንዲሁም በመንግሥት ሠራተኞች ነፃነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች በአንድ ልማታዊ መንግሥት ዲሞክራሲያዊነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩ ፋንቱ ትገልጻለች፡፡

የልሂቃኑ ውክልና ለመንግሥት ነው ወይስ ለሕዝቡ? የመንግሥት ሠራተኛ የሚሰጠው የኢኮኖሚና የማኅበራዊ አገልግሎት ተቀባይነት የሚያገኘው በሕዝባዊ ምርጫ ነው ወይስ ለመንግሥት በሚሰጠው ውጤት? መሠረታዊ ሕጎች የአብዛኛው ሕዝብ ስምምነት ይንፀባረቅባቸዋል ወይ? ሚዲያውና የሲቪል ማኅበረሰቡ ተጠሪነት ለሕዝቡ ወይስ ለልማታዊ መንግሥቱ? ለሚሉት ጥያቄዎች የሚሰጥ መልስ የአንድን አገር ዲሞክራሲያዊነት የመወሰን ኃይል እንዳላቸው ፋንቱ ታስረዳለች፡፡

አቶ እያሱ መኮንን የኢዴፓ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ አቶ እያሱ በልማት አስፈላጊነትና ልማት ከዲሞክራሲ ጋር ባለው ትስስር እምነት እንዳላቸው ቢገልጹም፣ ኢሕአዴግ ዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት ስለመመሥረቱ ግን አይስማሙም፡፡ ‹‹መንግሥት አድራጊ ፈጣሪ ሆኗል፡፡ የፈለገውን ሴክተር ያስፋፋል፤ ያልፈለገውን ይተዋል፡፡ የሚፈልገውን ብቻ ነው እየደገፈ ያለው፡፡ አስተሳሰቡ ከዲሞክራሲ አንፃር እንቅፋት ነው፤›› ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡

ዲሞክራሲያዊ ልማት ለኃይለ ማርያም

አቶ መለስ የዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት አፍላቂና ተከላካይ ነበሩ፡፡ በሒደቱ ጥልቅ የሆነውን የኢኮኖሚ አስተሳሰባቸውን ተጠቅመዋል፡፡ አሁን ኢትዮጵያን የሚመሩት አቶ ኃይለ ማርያም ፈጣን ተማሪነታቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቶ አያውቅም፡፡ በሰነድ ከወረሱት የዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት የመለስ ትንታኔዎች ባሻገር በቅርበት አብረው በመሥራት ያከማቹት ልምድ ጠቃሚ ነው፡፡ በተጨማሪም የአቶ መለስ የኢኮኖሚ አማካሪዎች አስፈላጊነት አሁን መጨመሩም አያጠራጥርም፡፡

ነገር ግን ከላይ ከተገለጹት መጠነ ሰፊ ጥያቄዎችና መከራከርያ ነጥቦች አኳያ ይህ ርዕዮተ ዓለም ፈተናዎች ያጋጥሙታል፡፡ በተለይ ዲሞክራሲን ያረጋገጠ ልማት ለመቀጠል ከአፋዊና ሰነዳዊ መከራከሪያዎች ይልቅ ተግባራዊ ምላሽ ይፈለጋል፡፡

አቶ አብርሃም ከበደ የኢትዮጵያ ልማታዊ መንግሥት ዲሞክራሲያዊነት ጥያቄ የፖሊሲ ወይም የሕግ ሳይሆን የተግባራዊነት በመሆኑ አቶ ኃይለ ማርያም ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጫና እንደሚበረታባቸው ይገልጻሉ፡፡ ቻርልስ አቡግሬ አቶ ኃይለ ማርያም የዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥትን ርዕየተ ዓለም መተግባር አለመተግባራቸው በጊዜ ሒደት እንደሚታወቅ ይገልጻሉ፡፡ ዶ/ር መድኅኔ ታደሰ አቶ መለስ የልማታዊ መንግሥትን መሠረት ቢጥሉም በእሳቸው ጊዜ ቦታ ያልነበረው ዲሞክራሲ በአቶ ኃይለ ማርያም በአስቸኳይ ቦታው እንዲቀየር ይጠይቃሉ፡፡ አቶ እንዳልካቸው ገረመው ያለ መለስ ልማታዊ መንግሥትን መግፋት አስቸጋሪ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በተለይ አፈጻጸሙ ላይ እንዲሁም የሐሳቡን አፍላቂ ሐሳብ ለመጠበቅ የሚደረገው ጥረት አለመግባባት እንደሚፈጥር ያላቸውን ግምት ይሰጣሉ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም የሐሳቡን አመንጪ የአቶ መለስን ሐሳብ ለመረዳት የተሻለ ዕድል ቢኖራቸውም፣ ከንባብና ከመለስ ጋር ካደረጉት ውይይት በዘለለ የሚመጡ የመርህና የአፈጻጸም ልዩነቶችን ለማስታረቅ መቸገራቸው እንደማይቀር የሚገልጹት አቶ እያሱ መኮንን ደግሞ ዲሞክራሲን ባረጋገጠ ሁኔታ ለውጥ ያደርጋሉ ብለው እንደማይጠብቁ ግን ይገልጻሉ፡፡    
http://www.ethiopianreporter.com/politics/295-politics/8247-2012-10-27-08-49-55.html

Comments

Popular Posts

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የመንግሥት ስልጠና የምርጫ ቅስቀሳ አካል ነው ብሏል  የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ለምን ወጣ መባሉ ተገቢ አይደለም - ምርጫ ቦርድ ምርጫ ቦርድ ከኢህአዴግ ተፅዕኖ ሙሉ ለሙሉ ነፃ መሆኑ ሳይረጋገጥና የምርጫ አፈፃፀም ችግሮች ሳይወገዱ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ለማወጅ መዘጋጀቱ ተገቢ አይደለም ሲል ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመሩት ኢማዴ-ደህአፓ ተቃወመ፡፡ መንግስት፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎችን ጨምሮ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየሰጠ ያለው ስልጠና የምርጫ ቅስቀሳ አካል ነው ሲልም ፓርቲው ኮንኗል፡፡  የኢትዮጵያ ማህበረ ዴሞክራሲ ደቡብ ህዝቦች አንድነት ፓርቲ ሰሞኑን ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባስገባው ግልፅ ደብዳቤ፤ ያለፉት አገር አቀፍና የአካባቢ ምርጫዎች ከመካሄዳቸው በፊት በምርጫ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር የሚወያይበት መድረክ እንዲዘጋጅ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም እስካሁን ከቦርዱ የተሰጠ ተግባራዊ ምላሽ የለም ብሏል፡፡  ሃገሪቱ “በአንድ አውራ ፓርቲ” ብቸኛ ቁጥጥር ስር መውደቋ አደገኛና አሳሳቢ ነው ያለው ፓርቲው፤ የመድብለ ፓርቲ ስርአት የመገንባት ተስፋችን ጨርሶ እንዳይከስም ቦርዱ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የሚካሄድበትን ሁኔታ ለመፍጠር ገዥው ፓርቲና ሃቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚወያዩበት መድረክ እንዲያመቻች በህግ ስልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድ የገባውን ቃል በማጠፍ መድረኩን ሳያመቻች የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀቱ ፋይዳ የለውም ብሏል - ፓርቲው፡፡  ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በተሻሻለው የምርጫ ህግ፣ ለቦርዱ የተሰጠውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ የማስተባበር ስልጣን ለመቀማት ታማኝ ፓርቲዎችን በተቃዋሚ ስም አሰባስቦ “የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ” በመፍጠር የምርጫ ውድድር አሯሯጭ አሰልፏል ሲ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

የለበሰው ያደፈ ቁምጣና ሹራብ ከቅዝቃዜው አላዳነውም፡፡ ካፊያው ልብሱን አርሶታል፡፡ ሽው እያለ ከሐይቁ የሚነሳው ነፋስ የሚፈጥረው ቅዝቃዜ ያንቀጠቅጠዋል፡፡ የተጫማው ያረጀ ሲሊፐር እግሩን ከምንም አላዳነውም፡፡ በባዶ እግሩ የሚራመድ ያህል ጨቅይቷል፡፡ ተደባዳቢ ይመስል ፊቱ የተሞነጫጨረ ነው፡፡ ገና 12 ዓመቱ ቢሆንም፣ ቁመናው እንደ ትልቅ ሰው ግዙፍ ነው፡፡ የሚለብሰውን እንደ ልቡ ባያገኝም፣ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ቤሳቢስቲን የሌላቸው ወላጆቹን አያስቸግርም፡፡ ከቤተሰቦቹ ጋር ከሚኖሩበት ታቦር ተራራ ጀርባ ወዳለው ሐዋሳ ሐይቅ ከወረደ እንኳንስ የራሱን የቤተሰቦቹንም የዕለት ጉርስ የሚሸፍንበት ገንዘብ አያጣም፡፡ የአስጎብኚነት ዕውቀት፣ ከሐይቁም ውስጥ ዓሳ የሚያጠምድበት መረብም ሆነ ፈቃድ የለውም፡፡ ሙሉቀን (ስሙ ተቀይሯል) እና ጓደኞቹ ሐይቁን ለመጎብኘት የሚሄዱ ጎብኚዎች በካሜራቸው ጥሩ ፎቶ እንዲያስቀሩ ድባቡን የማሳመር ሥራ ይሠራሉ፡፡ ካሜራውን ይዞ ቁጭ ብድግ እያለ ጥሩ ፎቶ ለማንሳት ጥረት የሚያደርግ ሲያዩ፣ ቆርጠው የያዙትን የዓሳ ሥጋ ይዘው ጠጋ ጠጋ ይላሉ፡፡ ቁርጥራጩን የዓሳ ሥጋ ምግብ ለሚቀሙት አባኮዳዎች ሻሞ ይላሉ፡፡ የተወረወረላቸውን ቀድመው ለመቅለብ አባኮዳዎቹ ክንፋቸውን እየመቱ ወደ ላይ ብድግ ይላሉ፡፡ የናሽናል ጆግሪፊ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ያነሱት ዓይነት ፎቶዎች ሳያስቡት ያነሳሉ፡፡ በሁኔታው ተደስተው ደጋግመው ድንቅ ፎቶዎችን ለመውሰድ ሲዘጋጁ እነ ሙሉቀንም አጀንዳቸውን ይፋ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ አቶ ዳዊት አብርሃም ‹‹አንዱን ዓሳ በአሥር ብር ገዝቼ ነው እንዲህ የማዘጋጀው፤›› በማለት በቅድሚያ  መረጃ ይሰጣሉ፡፡ ለቀጣዩ ዜና በዚህ መልኩ እንዲዘጋጁ ካደረጉ በኋላ፣ ሌሎች ሰዎች መቶም ሁለት መቶም ብር እንደሚሰጧቸው ቀለል

Sidama: the Luwa and the Anga Culture and their Social Implications

By Wolassa Kumo 1. Introduction In my previous articles, I mentioned the Sidama grand social constitution Seera, and various sub constitutions which derive from this grand constitution. We have also seen that all social constitutions or Seera in Sidama were based on the Sidama moral code of halale, the true way of life. In this socio-cultural and socio-political system, the role of the elders was very important. Elders were bestowed with the power of enforcing the Seera and referring the recalcitrant to Magano or God if he/she refuses to abide by the Seera. The power of elders in the Sidama society was not based on a simple age count as is the case in most modern societies. The Sidama elder is more the product of various social processes through which he passes than the product of a simple aging. For a person to become a recognised elder with authority in Sidama, he has to become a Cimeessa (respected elder with authority) or Cimeeyye for many respected elders. There are three importa