በቡና አላላክ ላይ የወጣው አወዛጋቢ መመርያ ተሻረ

The short-lived directive in the Ethiopia coffee sector
ንግድ ሚኒስቴር ከህዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ሌላ የተለየ ፈቃድ ከሚኒስቴሩ ካልተሰጠ በስተቀር የኢትዮጵያ ቡና በብትን በኮንቴይነር እንዲላክ ያወጣውን አወዛጋቢ መመርያ ማንሳቱን አስታወቀ፡፡ መመርያው ተግባራዊ እንዲሆን በተወሰነ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ነው የተሻረው፡፡  

የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ባለፈው ሐሙስ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር የቦርድ አባላትን ሰብስበው ካነጋገሩ በኋላ፣ ቡና በብትን ብቻ ይላክ የሚለው መመርያ ተቀልብሶ በጆንያና በብትን መላክ እንደሚቻል መፈቀዱን ነግረዋቸዋል፡፡ 

ቡና ላኪዎቹ በበኩላቸው ምንም እንኳ በብትን መላኩ በሚያስገኘው ጠቀሜታ ላይ ጥያቄ ባይኖራቸውም፣ ገዢዎች እስኪቀበሉትና ፍላጎት ኖሯቸው በብትን መቀበል መፈለጋቸውን እስኪያስታውቅ፣ ለብትን አላላክ ሥርዓት የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች እስኪሟሉ ድረስ ግን በብትንም በጆንያም መላክ ሊፈቀድ እንደሚገባ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ 

በብትን የመላክ መመርያው የተነሳው እነዚህን እውነታዎች ከግምት በማስገባት እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡ መመርያው ከተነሳ በኋላ በብትን መላክ እስኪለመድና ተቀባይነት እስኪያገኝ ድረስ በጆንያ መላኩ እንደ ሽግግር ወቅት ተደርጎ ቢፈቀድም፣ ይህ የሽግግር ወቅት የተባለው በጊዜ ገደብ አለመቀመጡን ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ 

ለመመርያው መውጣት ሲሰጡ ከነበሩ ምክንያቶች አንዱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አምነውበት ተቀባይነት ያገኘ አሠራር በመሆኑ፣ የዝግጅት ጊዜው አምና ተጠናቆ ዘንድሮ ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራ ሊገባበት እንደተቻለ መሆኑን ንግድ ሚኒስቴር ለሁሉም ላኪዎች ያሰራጨው ደብዳቤ ያመለክታል፡፡ 

በሚኒስትር ዴኤታው አቶ ያዕቆብ ያላ ተፈርሞ የወጣው መመርያ እንደሚያትተው፣ ቡናን በብትን በኮንቴይነር ውስጥ አሽጎ መላክ የኢትዮጵያ የኤክስፖርት አስተሻሸግን ዘመናዊ የሚያደርግና የአላላክ ደረጃውንም የሚያስጠብቅ ነው፡፡ 

በብትን ሲላክ ጥራቱ እንደተጠበቀ የሚጓጓዝበት፣ ከቅሸባ ስርቆት የሚድንበት፣ የቡና ገዢዎችን ጆንያ የማስወገድ ወጪ የሚቀንስበት አጋጣሚ ይፈጥራል የሚለው መመርያው፣ ቡና ላኪዎችም ለጆንያ የሚያወጡት ወጪን ያስቀራል በማለት ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ ከዚህም ባሻገር በጂቡቲ ወደብ የሚወጣውን ወጪ በመቆጠብና የጭነት ማጓጓዣ ጊዜን በማሳጠር ለገዢና ለሻጭ ተጨማሪ ጥቅም እንደሚያስገኝ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ 

ጥቂት የማይባሉ ቡና ላኪዎች ግን ቡናን በብትን መላክ ይሰጣል የሚባለው ጠቀሜታ የተጋነነ መሆኑንና በየትኛውም አገር በጆንያና በብትን መላክ የተለመደ እንደሆነ በመግለጽ ሲቃወሙት፣ በተለይ የኢትዮጵያ ዋነኛ የሚባሉ ቡና ገዢዎች በብትን ብቻ ግዙ መባላቸውን አንቀበልም እንዳሉ በመግለጽ ለሚኒስቴሩ አስታውቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡ 

ቡናን በብትን መላክ ማለት በአንድ ኮንቴይነር ውስጥ በሚዘጋጅ ከረጢት ‹‹ብሎወር›› በሚባል ማሽን ቡናውን መገልበጥ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ቡናን በብትን ለመላክ የሚያስችል የተሟላ መሠረተ ልማት እንደሌለም ይስማሙበታል፡፡  

No comments