በደቡብ ክልል የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የ13 ሆቴል ባለንብረቶችን በተጨማሪ እሴት ታክስ (በቫት) ማጭበርበር በመጠርጠራቸው በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ታወቀ፡፡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ባለሆቴሎች መካከል የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ማረጋጫ ሰርተፍኬት ያላቸው ይገኙበታል፡፡ የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የመናኸሪያ ክፍለ ከተማ አዛዥ ኢንስፔክተር በየነ ባናታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሆቴል ባለንብረቶቹና ተወካዮቻቸው የተያዙት ለመንግሥት ማስገባት የነበረባቸውን ተጨማሪ እሴት ታክስ በማጭበርበር ተጠርጥረው ነው፡፡ ኢንስፔክተር በየነ እንደሚሉት፣ በመናኸሪያ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የብሉ ናይል፣ የታደሰ እንጆሪ፣ የሲዳማ ውበት ሆቴሎች ሥራ አስኪያጆችና ገንዘብ ተቀባዮች በአጠቃላይ አሥር ሰዎች /አራት ሴትና ስድስት ወንድ/፤ እንዲሁም የሐሮኒ ኢንተርናሽናል፣ የኢቪኒንግ ስታር፣ የበሹ ጫምበላላ፣ የሻሸመኔ ሪፍት ቫሊ፣ የወላይታ ሶዶና የአርባ ምንጭ ቱሪስት ሆቴሎች ኃላፊዎችና ገንዘብ ተቀባዮች ናቸው፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሻሸመኔ ሪፍት ቫሊ፣ የወላይታ ሶዶና የአርባ ምንጭ ቱሪስት ሆቴሎች ባለንብረቶች በተመሳሳይ የደረሰኝ ቁጥር ቫት ሲሰበሰቡ ቆይተው ለመንግሥት ገቢ ማድረግ የሚገባቸውን አሥራ ሁለት ሚሊዮን ብር ማጭበርበራቸው በጥቆማ ተደርሶባቸው መሆኑን፣ የእነዚሁ ሆቴሎች ባለሀብቶች በደረጃ አንድ የኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሠማሩና በተመሳሳይ የማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡ የብሉ ናይል፣ የኢቪኒንግ ስታር፣ የሲዳማ ውበት፣ የቤራ፣ የዳህላክና የታደሰ እንጆሪ ሆቴሎች ባለቤቶች በመሰወራቸው ሥራ አስኪያጆችና ገንዘብ ተቀባዮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ምንጮች ለሪፖርተር አክለው ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ የአሥ
It's about Sidaama!